የቱርክ ባለሃብቶች በኢትዮጵያ የተፈጠረውን የኢኮኖሚ ዕድል እንዲጠቀሙ ጥሪ ቀረበ

118
አዲስ አበባ ነሀሴ 10/2010 የኢትዮጵያ መንግስት በኢኮኖሚው እያደረገ ያለው ማሻሻያ ለቱርክ ባለሀብቶች መልካም አጋጣሚ የሚፈጥር መሆኑን በኢትዮጵያ የቱርክ አምባሳደር ፋቲህ ኡሉሶይ ገለጹ። አምባሳደሩ ይህን ያሉት ሰሞኑን በቱርክ ርዕሰ መዲና አንካራ በተደረገው 10ኛው የሁለቱ አገራት የአምባሳደሮች ስብሰባ ላይ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት ለኢዜአ አስታውቋል። አምባሳደር ፋቲህ በኢትዮጵያ በቅርቡ በህዝብ ይዞታ ስር የነበሩ ዘርፎች በከፊልና በሙሉ ወደ ግሉ ክፍለ-ኢኮኖሚ እንዲዛወሩ የሚያስችል የማሻሻያ ሃሳብ ይፋ መደረጉን አድንቀዋል። የቱርክ ባለሃብቶች ጉዳዩን በቅርበት እንዲከታተሉና ዕድሉን እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበው በመንግስታቸው በኩልም ፍላጎት ላላቸው ባለሃብቶች አስፈላጊውን ድጋፍ ለመስጠት ሰፊ ዝግጅት መደረጉን አስታውቀዋል። አምባሳደር ፋቲህ በኢትዮጵያ በኩል የኤሌክትሮኒክስ ቪዛ መስጠት የተጀመረ መሆኑ ወደ ቱርክ የሚደረጉ የቢዝነስ ጉዞዎችን በእጅጉ እያቀላጠፈ መሆኑንም አስረድተዋል። ቱርክ በኢትዮጵያ ያላትን ቢዝነስና ኢንቨስትመንት ማስፋት እንደምትፈልግም አመልክተዋል። የአገራቸው የባህል ተቋም የሆነው ተርኪሽ ማሪፍ ፋውንዴሽን በቅርቡ በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቱን ለመክፈት ዝግጅት ማጠናቀቁን ይፋ አድርገዋል። የባህል ተቋሙ ጽህፈት ቤቱን የሚከፍተው የሁለቱ አገራትን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ይበልጥ ለማጠናከር እንደሆነም ተናግረዋል።      
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም