ኢሬቻን በፍቅር፣ በይቅር ባይነት፣ በመተሳሰብ እና በአንድነት እናከብረዋለን

መስከረም 19/2014 (ኢዜአ) ኢሬቻን በፍቅር፣ በይቅር ባይነት፣ በመተሳሰብ እና በአንድነት እንደሚያከብሩ አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ከአዲስ አበባ ከተማ የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አመራሮችና ሠራተኞች ተናገሩ ።

ከመዲናዋ የተለያዩ ተቋማት የተውጣጡ አመራሮችና ሠራተኞች ቀጣይ የኢሬቻ በዓል አከባበርን አስመልክቶ የፓናል ውይይት አድርገዋል።

በውይይቱም የመነሻ ጽሑፍ የቀረበ ሲሆን አባ ገዳዎች፣ ሃደ ስንቄዎች፣ የአገር ሽማግሌዎችና ሌሎች እንግዶች ታድመዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ምክትል ኃላፊ አቶ አለማየሁ እጅጉ፤  የክረምት ወራት ተገፎ ብርሃን የሚመጣበትን የኢሬቻ በዓል በፍቅር፣ በይቅርባይነት፣ በመተሳሰብ እና በአንድነት ለማክበር ተዘጋጅተናል ብለዋል።

በዓሉ በአዲስ አበባ ሲከበር ወደ መዲናዋ ለሚመጡ እንግዶች ነዋሪው ተገቢውን አቀባበል በማድረግ አክበሮትና ፍቅራቸውን ማሳየት አለባቸው ብለዋል።

የውይይት የመነሻ ጽሑፍ ያቀረቡት የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ዘላለም ሙላቱ፤ የኦሮሞ ህዝብ የምስራቅ አፍሪካ አገሮችን በባህል፣ በቋንቋና በኃይማኖት በማስተሳሰር ለዓመታት አብሮት የዘለቀ የሥልጣኔ ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።

ለዓመታት አብሮት በዘለቀው ባህልና እሴት ዴሞክራሲያዊነትን በተላበሰው የአኗኗር ሂደቱ በጉዲፈቻና ሞጋሳ  ባህሉን ለሌሎች ሲያጋራ የኖረ የቀደምት ታሪክ ባለቤት መሆኑን ጠቅሰዋል።

ኢሬቻ በሰው ልጅና ፍጡራን በሰማይና በምድር መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያጸናበት የሚያመሰግንበትና በቀጣይም በአንድነት ተሰናስሎ ምስጋና የሚያቀርብበት ሥርዓት መሆኑን አብራርተዋል።  

ለኢዜአ ሐሳባቸውን ያካፈሉ የፓናል ውይይቱ ተሳታፊዎች፤ የኦሮሞ ህዝብ ሁለንተናዊ መገለጫ የሆነው የኢሬቻ በዓል ሲከበር በፍቅር፣ በይቅር ባይነት፣ በመተሳሰብ እና በአንድነት መሆን አለበት ብለዋል።

ኢሬቻ በመጪው ቅዳሜ በአዲስ አበባ ሲከበር በማግስቱ እሑድ በቢሾፍቱ ከተማ ይከበራል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም