ቀጥታ፡

የነዋሪዎችን ህይወት ትርጉም ባለው መልኩ ለማሻሻል እንሰራለን - ከንቲባ ከድር ጁሀር

መስከረም 19 ቀን 2014 (ኢዜአ) "የነዋሪዎችን ህይወት ትርጉም ባለው መልኩ ለማሻሻል እንሰራለን" ሲሉ በድሬዳዋ አስተዳደር ምክር ቤት አዲስ የተመረጡት ከንቲባ ከድር ጁሀር ገለጹ።


አዲስ ተሿሚው ከንቲባ ዛሬ በምክር ቤቱ ቃለ መሃላ ከፈፀሙ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ የነዋሪውን ህይወት ለማሻሻል እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

"ከድሬዳዋ ህዝብ ጋር በአንድነት፣ በትብብር እና አብሮነት ችግሮችን እየፈታን ስኬት ለማስመዝገብ ዝግጁ ነን" ብለዋል።

በመጪዎቹ አምስት ዓመታት ድሬዳዋን የኢንዱስትሪ ማዕከል ለማድረግም እንደሚሰራ ጠቁመዋል።

የኑሮ ውድነት ችግርን መፍታት፣ የገጠር ህዝብን የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ እንዲሁም የወጣቶች የስራ እድል ፈጠራ ትኩረት እንደሚሰጠው ገልጸዋል።

ከህዝቡ ጋር በመተባበር የኢኮኖሚ ችግሮች በመፍታት ሂደትም በተለይም የገጠሩን ህዝብ ህይወት ለማሻሻል የመስኖ ልማት እና የእንስሳት ሃብት ልማት ላይ በሰፊው የመስራት እቅድ እንዳለ ጠቅሰዋል።

"አካል ጉዳተኞች እና አረጋዊያን በልማት ተሳታፊና ተጠቃሚ እንዲሆኑ ይደረጋል" ያሉት ከንቲባው፤ ድሬዳዋን ለኢንቨስትመንት ምቹ፣ ተመራጭ እና ተፈላጊ ለማድረግ ሁሉም መረባረብ እንዳለበት አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም