በኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ባንዲራ እና ሌሎች በዓሉን የማይወክሉ ነገሮችን መያዝ የተከለከለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ባንዲራ እና ሌሎች በዓሉን የማይወክሉ ነገሮችን መያዝ የተከለከለ ነው
መስከረም 19/2014 (ኢዜአ) በኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ባንዲራ እና ሌሎች በዓሉን የማይወክሉ ነገሮችን መያዝ የተከለከለ መሆኑን የበዓሉ አከባበር የቴክኒክ ኮሚቴ አስታወቀ።
የበዓሉን አከባበር የሚያስተባብረው የቴክኒክ ኮሚቴ ዛሬ ለመገናኛ ብዙሃን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል።
የኮሚቴው አስተባባሪ አቶ ከበደ ዴሲሳ፤ በአዲስ አበባ እና በቢሾፍቱ ለሚከበረው የኢሬቻ በዓል አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል።
በኢሬቻ ክብረ በዓል ላይ የፖለቲካ ፓርቲ ባንዲራ እና ሌሎች በዓሉን የማይወክሉ ነገሮችን መያዝ የተከለከለ መሆኑን ተናግረዋል።
በዓሉ በሠላም እንዲከበር ሕዝቡ የተለመደ ትብብሩን ማድረግ እንደሚጠበቅበት ገልጸው፤ በዓሉን ለማክበር የሚመጣ ሁሉ ለኮቪድ-19 ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረገ መሆን ይኖርበታል ብለዋል።
ከበዓሉ በፊት የተለያዩ ጥናቶች እንደሚቀርቡና ፎረሞች እንደሚዘጋጁም ጠቁመዋል።
የኢሬቻ በዓል ከኦሮሞ ሕዝብ በተጨማሪ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች እንደሚሳተፉበት ይጠበቃልም ብለዋል።
በዓሉ የኢትዮጵያዊያን የፍቅርና አብሮነት መገለጫ ሆኗል ያሉት አቶ ከበደ ፤የባህል ልውውጥና እና የትውውቅ መድረክ መሆኑንም ጠቅሰዋል።
በበአሉ ሰበብ የራሳቸውን የፖለቲካ ፍላጎት ለማንጸባረቅ የሚፈልጉ አንዳንድ አካላት ስላሉ ህብረተሰቡ በጥንቃቄ ሊከታተላቸውና ሊያጋልጣቸው ይገባል ብለዋል።
ኢሬቻ የሰላም፣ የምስጋና፣ የአብሮነት እና የአንድነት መገለጫ በመሆኑ ከዚህ በተቃራኒ የፖለቲካ ፍላጎት ማንጸባረቂያ ቦታ ለማድረግ የሚፈልጉትን ህብረተሰቡ ሊከላከላቸው እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ኢሬቻ ማለት ማምለክ እና ማመስገን ማለት ነው፤ ይሄን ስላደረግክልኝ፣ ከክረምት ወደ በጋ /ብራ/ ስላሸጋገርከኝ አመሠግናለሁ እየተባለ ፈጣሪ የሚመሰገንበት በዓል ነው።
በኢሬቻ በዓል ሰዎች እርጥብ ሳር ይዘው ወደ መልካ /ወንዝ/፣ ሃይቅ በመሄድ ፈጣሪያቸውን ያመሰግናሉ እንዲሁም ይለምናሉ።
የዘንደሮው የኢሬቻ በዓል መስከረም 22 በአዲስ አበባ እንዲሁም መስከረም 23 ቀን 2014 ዓ.ም በቢሾፍቱ ይከበራል።