ቀጥታ፡

ሰላምና አንድነት የማምጣትን ስራ ከሚያደናቅፉ ግጭቶች መጠንቀቅ ተገቢ ነው - የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ አንድነት የጋራ ኮሚቴ

አዲስ አበባ ነሃሴ 10/2010 በአንዳንድ አካባቢዎች በሙስሊሞች መካከል እየተፈጠሩ ያሉ ግጭቶች ዘላቂ አንድነት ለማምጣት በሚሰራው ስራ ላይ እንቅፋት ስለሚፈጥር ሁሉም ሊጠነቀቅ እንደሚገባ የኢትዮጵያ ሙስሊሞች ተቋማዊ አንድነት የጋራ ኮሚቴ አሳሰበ። ኮሚቴው ዛሬ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰሞኑን በወሎ ኮምቦልቻና ደሴ የተፈጠረው ግጭት በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት ሲያደርስ አንድን ሰው ለሞት ዳርጓል። የኮሚቴው ሰብሳቢ ተቀዳሚ ሙፍቲ ሃጅ ኡመር እድሪስ በመግለጫው እንዳሉት "አላህ በቁርዓን ስለ ሰላም፣ ስለ አንድነት፣ ስለ መተባበር፣ ስለ መወያየትና መደማመጥ ብዙ ብሏል፤ ትልቅ ቦታም ሰጥቶታል።" በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ የመጡት መሪም ለነዚህ ነገሮች ቅድሚያ ሰጥተን በሰላምና አንድነት እንድንኖር ሌት ከቀን የሚሰብኩ ናቸው ብለዋል። ይህንኑ እውን ለማድረግም በሙስሊሙም ሆነ በክርስቲያን ቤተ እምነቶች ውስጥ ያሉ ኩርፊያዎችን ለማጥፋትና ወደ አንድነት ለማምጣት ብዙ እየሰሩ ነውም ብለዋል። ሆኖም ሰሞኑን በተለያዩ አካባቢዎች ከትንንሽ ልዩነቶች ተነስቶ ወደ ግጭት የማምራት ያልተገባና የሚያሳዝን እንቅስቃሴ እየታየ መሆኑን ገልጸዋል። ሰሞኑን በወሎ ኮምቦልቻና ከሚሴ አካባቢ በታየው ግጭትና አላስፈላጊ የህይወት መጥፋትና አካል ጉዳት ማዘናቸውን በመግለጽ። ተግባሩ አሁን አዲሱ ኮሚቴ የጀመረውን ስራ የሚያደናቅፍና የሚያጓትት በመሆኑ የተለየ ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል ያሉት ደግሞ የኮሚቴው አባል ኡስታዝ አቡበከር አህመድ ናቸው። ከዚህም ባለፈ መሰል ግጭቶች ''እኔ ትክክል፤ እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን'' ከሚሉ አስተሳሰቦች የሚመነጩ ናቸው ያሉት የኮሚቴው ቃል አቀባይ  ኡስታዝ ካሚል ሻምሱ  "የሰው መብትም መጋፋት ስለሆነ ስህተት ነው ብለዋል። " ይህ ደግሞ በኃይማኖቱ በጣም የተወገዘና ከእምነት መስመሩ የሚያስወጣ ተግባር በመሆኑ የተለየ ጥንቃቄ በማድረግ ኮሚቴው ለጋራ አንድነት ይበጃል የሚለውን መፍትሄ ይዞ እስኪመጣ ድረስ  ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠብቅ የኮሚቴው ሰብሳቢ አሳስበዋል። ከዚህ በፊት የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤትና የሙስሊም መፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ጋር ካደረጉት ውይይት በኋላ የሙስሊሙ ህብረተሰብ አንድነት ማጠናከር ላይ የሚሰራ ዘጠኝ አባላት የያዘ ኮሚቴ መቋቋሙ ይታወሳል።  
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም