ቻይና ባለፉት 3 አመታት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ በኢትዮጵያ 118 ሺህ የተማሪ ቦርሳዎችን ድጋፍ አድርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ቻይና ባለፉት 3 አመታት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ በኢትዮጵያ 118 ሺህ የተማሪ ቦርሳዎችን ድጋፍ አድርጋለች

መስከረም 19/2014 (ኢዜአ) ቻይና ባለፉት ሶስት አመታት 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር ወጪ በማድረግ በኢትዮጵያ 118 ሺህ የተማሪ ቦርሳዎችን ድጋፍ ማድረጓን የትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የቻይና ፋውንዴሽን ከአሊባባ ጋር በመተባበር ለመለገስ ቃል ከገባው 118 ሺህ የተማሪዎች ቦርሳ የመጨረሻውን 20 ሺህ ቦርሳዎች ዛሬ ለትምህርት ሚኒስቴር አስረክቧል።
ቻይና ከ2012 ዓ.ም ጀምሮ ለሶስት ተከታታይ አመታት የዛሬውን ጨምሮ 118 ሺህ የደብተር መያዝ ቦርሳዎችንና ሌሎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ማበርከቷን የትምህርት ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጅነር ጌታሁን መኩሪያ ተናግረዋል።
የኮቪድ ወረርሽኝ በተከሰተበት ወቅት መምህራንን ብቻ ታሳቢ ያደረገ ከ300 ሺህ በላይ የኮቪድ ክትባቶችን ድጋፍ ማድረጉን ጠቅሰው በትምህርት ዘርፉ እያደረጉት ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።
የቻይና ፋውንዴሽን የኢትዮጵያ ተወካይ ሁዋንግ ቫውሽን ድርጅቱ በኢትዮጵያ ትምህርትን ጨምሮ በጤናው ዘርፍ በርካታ ስራዎችን ሲያከናውን መቆየቱን ገልጸዋል።
በዛሬው እለትም የመጨረሻውን ዙር 20 ሺህ ቦርሳዎችንና ተጨማሪ አጋዥ ቁሳቁሶችን ማበርከቱን ተናግረዋል።
ለድጋፉ 2 ነጥብ 4 ሚሊዮን ዶላር የሚጠጋ ወጪ መደረጉን ገልጸው ኢትዮጵያ በትምህርት ዘርፍ በምትሰራቸው ስራዎች ቻይና ድጋፏን አጠናክራ እንደምትቀጥል አረጋግጠዋል።
ድጋፉ በተለያዩ ክልሎች ለሚገኙ ተማሪዎች የሚከፋፈል ሲሆን የኦሮሚያ ክልልና የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮዎች ዛሬ ድጋፉን ተረክበዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ግርማ ባይሳ በክልላቸው ከ10 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች መኖራቸውን ጠቅሰው ከነዚህ መካከል 100 ሺህ ተማሪዎች የተለያዩ ድጋፎች የሚሹ ናቸው ብለዋል።
በመሆኑም ባለፉት ሁለት አመታት ፓንዳ ፓርክ ፋውንዴሽን ያደረገልን ድጋፍ ተማሪዎቻችን ትምህርት እንዳያቋርጡ ከፍተኛ እገዛ አበርክቶልናል ብለዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ምክትል ቢሮ ሃላፊ አቶ ዳኘው ገብሩ፤ በትምህርት ላይ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው ተናግረው የቻይና መንግስት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።
ድጋፉ የትምህርት ምጣኔ መዝለቅን የሚያረጋግጥ ከመሆኑ ባለፈ የተለያየ የኢኮኖሚ ደረጃ ላይ የሚገኙ ተማሪዎች የበታችነት ስሜት እንዳይፈጠርባቸው ይረዳል ብለዋል።
"ተማሪዎችን መደገፍ ሃገርን መገንባትና ሃገርን መስራት" በመሆኑ አቅሙ ያላቸው ግለሰቦች ሁሉ ዘርፉን እንዲደግፉም ጥሪ አቅርበዋል።
ድጋፉ የአዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ፣ ለአማራ፣ ኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች መሰጠቱ ተገልጿል።