የነገ ቤታችንን ዛሬ እንስራ - ኢዜአ አማርኛ
የነገ ቤታችንን ዛሬ እንስራ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 19/2013 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ከሚገኙ አረጋዊያን 23 በመቶ የሚሆኑት የተለየ ድጋፋ የሚሹ መሆናቸው ተገልጸ።
ይህ የተገለጸው የሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም የሚከበረውን ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ነው።
ሚኒስትር ዴኤታው አቶ ጌታቸው በዳኔ በኢትዮጵያ 6 ነጥብ 8 ሚሊዮን አረጋዊያን መኖራቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህ መካከልም 23 በመቶ የሚሆኑት መጠለያ የሌላቸውና በቂ ምግብ የማያገኙ፤ ለተለያዩ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ችግሮችም የተጋለጡ መሆናቸውን ነው የተናገሩት።
በዋናነት ለዚህ ችግር እንዲጋለጡ ያደረጋቸው ደግሞ ተገቢ ማኅበራዊ ዋስትና የሌላቸው መሆኑ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
ሚኒስቴሩ ባለፉት ሶስት ዓመታት የአረጋዊያንን ችግሮች ለማቃለል የተለያዩ ስራዎችን ማከናወኑንም ተናግረዋል።
ከእዚህም መካከል የአረጋዊያንን ጉዳይ የሚከታተል ራሱን የቻለ አደረጃጀት መፈጠሩን ጠቅሰዋል።
የአረጋዊያንን መብቶችና ጥቅሞች የሚያስጠብቅ ረቂቅ ሕግ እየተዘጋጀ መሆኑንና በአዲስ አበባ የአረጋዊያን ሁለገብ ማዕከል ለመገንባት ስራዎች መጀመራቸውን ነው አቶ ጌታቸው የገለጹት።
በኢትዮጵያ የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ አረጋዊያን ጥቂት መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የኢትዮጵያ አረጋዊያንና ጡረተኞች ብሔራዊ ማኅበር ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ክፍሌ ናቸው።
የማኅበራዊ ዋስትና ተጠቃሚ ያልሆኑ በርካታ አረጋዊያን ለችግር እንደሚጋለጡ ገልጸዋል።
በመሆኑም የአረጋዊያንን ችግር ለመፍታት የጡረታ ዋስትና ተጠቃሚነትን በማስፋትና የመንግስት አስፈጻሚ አካላትም ተገቢውን ትኩረት በመስጠት መብትና ጥቅማቸውን ማስከበር ይገባል ብለዋል።
ይህ ብቻውን በቂ ባለመሆኑም አረጋዊያን መብታቸው ተክብሮ ከልማት ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሁሉም ዕድሜው ሲገፋ የሚደርስበትን "የነገ ቤቱን ዛሬ መስራት አለበት" ሲሉም መልዕክት አስተላልፈዋል።
ለችግር የተዳረጉ አረጋዊያንን መደገፍና የሚመለከተው የመንግስት አስፈጻሚ አካልም ተገቢውን ትኩረት መስጠት እንዳለባቸውም አክለዋል።
ዓለም አቀፍ የአረጋዊያን ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ31ኛ ጊዜ በኢትዮጵያ ለ30ኛ ጊዜ "ሁሉን አቀፍ ማኅበራዊ ጥበቃ ለአረጋዊያን" በሚል መሪ ሃሳብ መስከረም 21 ቀን 2014 ዓ.ም በአዳማ ከተማ ይከበራል።