ቀጥታ፡

በምዕራብ ኦሞ ዞን ለሚካሄደው ምርጫና ህዝበ ውሳኔ ዝግጅቱ ተጠናቋል

ሚዛን አማን፤ መስከረም 19/2014( ኢዜአ) በምዕራብ ኦሞ ዞን ነገ ለሚካሄደው ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫና የደቡብ ምዕራብ የክልልነት ህዝበ ውሳኔ ዝግጅት መጠናቀቁን በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የዞኑ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት አስታወቀ።

ስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ በዞኑ ሰኔ 14/2014 በጸጥታ ችግር ምክንያት ሳይካሄድ መቆየቱ ይታወሳል።

የማስተባበሪያ ጽህፈት ቤቱ ሃላፊ ወይዘሮ ዮርዳኖስ ሸለመው ለኢዜአ እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወሰነው መሰረት ምርጫውና ህዝበ ውሳኔውን ለማካሄድ ዝግጅቱ ተጠናቋል።

በዚህም በዞኑ 176 ምርጫ ጣቢያዎች ምርጫና ህዝበ ውሳኔው ይካሄዳሉ ብለዋል።

በምርጫውና በህዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ 127 ሺህ 816 መራጮች መመዝገባቸውን ወይዘሮ ዮርዳኖስ አስታውቀዋል።

ለመኤኒት፣ ለሱርማ፣ ለዲዚና ለማጀቴ መደበኛ የምርጫ ክልሎች እንዲሁም መደበኛ ባልሆኑ የመኤኒት፣ ዲዚ፣ ዝልማሙና ሱርማ ልዩ የምርጫ ክልሎች  የምርጫ ቁሳቁስ መሰራጨታቸውን አስታውቀዋል።

በዞኑ በሚካሄደው ምርጫ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ(ኢዜማ)ና ብልጽግና ፓርቲዎች ዕጩዎቻቸውን ማቅረባቸውን ገልጸዋል።

የዞኑ ፖሊስ አዛዥ ኢንስፔክተር አሸናፊ ቸርዋል በበኩላቸው፤ ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር እንዲጠናቀቅ ዝግጅት ተደርጓል ብለዋል።

ምርጫ በሚከናወንባቸው የምርጫ ጣቢያዎች የምርጫ ቁሳቁስ ደህንነት ተጠብቆ እንዲደርስ መደረጉንም ጠቁመዋል።

የደቡብ ክልል ልዩ ኃይል አባላት፣ መደበኛ ፖሊስና የአካባቢው ሚሊሻዎች የምርጫው ሰላማዊነቱን ጠብቆ እንዲካሄድ ተቀናጅተው እየሰሩ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም