ቀጥታ፡

የፕሬዚዳንቱ ውንጀላ ‘የራሷ እያረረባት … ‘ ዓይነት ነው - አርቲስት ደበበ እሸቱ

የዴሞክራሲ ተሟጋች ነኝ ብለው ራሳቸውን የሚያሞካሹት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በመካሄድ ላይ ባለው የተባበሩት መንግሥታት ስብሰባ የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ "ዩናይትድ ኔሽን" በማለት ፈንታ ሁለት ጊዜ ግድፈት ፈፅመው ዩናይትድ ስቴትስ በማለት እርምት ሳያደርጉ ቀጥለዋል።

በዚሁ የመክፈቻ ንግግራቸው ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የተለያዩ አገሮችን ስለሰብዓዊ መብት ጥሰት ወቀሳ ሰንዝረዋል።ፕሬዚዳንት ባይደን ይህን በሚሉበትና ራሳቸውን የሰብአዊ መብት ጠባቂ አድርገው ሲያሞካሹ፣ በግዛታቸው ድንበር የሚካሄደውን ጥቁር አፍሪካውያንን ኢላማ ያደረገውን የሰብአዊ መብት ረገጣ ከምንም ሳይቆጥሩት በዝላይ አልፈውታል።

ፕሬዚዳንቱ በዚህ ንግግራቸው "የአሜርካ መንግስት የሰብአዊ መብት ገፈፋን አጥብቆ በማውገዝ በየትም ቦታ፣ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ፣ በማንኛውም ሰው ላይ እንዳይፈፀም ይከላከላል፣ ሌሎች አገሮችም ይህን እንዲያደርጉ እንመክራለን፣ ግዴታም ነው" ብለዋል።

የፕሬዚዳንቱ ዲስኩር ተደስኩሮ ሳያልቅ፣ በሚያስተዳድሩት አሜሪካ ድንበር ላይ አገራቸው ላይ በደረሰው የተፈጥሮ ጎርፍና አውሎ ንፋስ በፈጠረባቸው ቀውስ ሳቢያ መጠጊያ ፍለጋ የአሜሪካን መስተንግዶ በማመን የፈለሱትን የሄይቲ ተወላጆች፣ የባይደንን የሰብዓዊ መብት ተሟጋችነት ከተባበሩት መንግሥታቱ አዳራሽ ሳይወጡ ፉርሽ አድርጎባቸዋል።

በጣም የሚያሳዝነው ደግሞ ከመጠጊያ ፈላጊዎቹ መካከል ሕፃናት፣ እድሜያቸው የገፉ እና መውለጃ ቀናቸው የተቃረቡ የሚመስሉ እናቶች ነበሩባቸው፤ ይህ ነው ፕሬዚዳንት ባይደን እናከብረዋለን ሌሎችም ያለቅድመ ሁኔታ እንዲያከብሩ እንጠይቃለን በማለት የተኩራሩበት ሰብዓዊ መብት።

ሁኔታው በጥቁር ስደተኞች ላይ እንዲህ በከፋና ሰብአዊነት በጎደለው መልኩ መፈፀሙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ ሂዩማን ራይትስ ዎች፣ ዊን ዊዝ አውት ዎር እና ሌሎችም የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ድርጊቱን ከማውገዛቸውም በላይ ስለ ሰብአዊ መብት ተሟጋችነታቸው በዓለም መንግሥታት ማሕበሩ መክፈቻ ሥርአት ላይ ከደሰኮሩት ጋር የሚቃረን ተግባር በመሆኑ አስተዳደራቸው ከድርጊቱ እንዲቆጠብ መመርያ እንዲሰጡ በጥብቅ አሳስቧል።

ይህ ደግሞ ፕሬዚዳንቱ ያንጸባረቁት ሃሳብ ‘የራሷ እያረረባት የሰው ታማስላለች’ የሚለው የአገራችንን ብሂል ተግባራዊነትን ያሳያል።ፕሬዚዳንቱ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ በመግባት፣ በምንም መልኩ ተቀባይነት የሌለውን ‘እኔ ልዘዝ እናንተም ታዘዙ’ እስከዛሬም ሲከናወን የነበረው በዚህ አይነት በመሆኑ መለወጥ የለበትም አይነት ቀጭን ትእዛዝ እየጣሉ ነው።

ላለፉት 27+ ዓመታት የህወሃት ዘመነ አገዛዝ አሜሪካ እንደልቧና እንዳሻት በአገሪቱ ሁለንተናዊ ንብረት ላይ፣ አዛበታለች፣ በወቅቱ የነበረውንም ጦር በግል ቀጭን ትእዛዝ ጦርነቷን እንዲዋጋላት አዛበታለች። በሶማልያ በተካሄደው ጦርነት የአሜሪካ ጦር ዘምቶ በነበረበት ወቅት፣ የሶማልያ ጦረኞች በከተማው የአየር ክልል ጥቃት ሊከፍት ሲያንዣብብ በሶማልያ የሰራዊት አባላት ተመቶ ሲወድቅ አብራሪው ህይወቱ ያልፋል።

የሶማልያ ነዋሪዎችም የአብራሪውን አስከሬን በሞቃድሾ አደባባይ ሲጎተት ቪድዮ በማንሳት በአሜሪካ ላሉ የቴሌቪዥን ጣቢያዎች እንዲደርስ አድርገው ለሕዝብ በመታየቱ የአሜሪካ እናቶች ‘ልጆቻችንን መልሱ’ ጥያቄ ሰላማዊ ሰልፍ በመካሄዱ፣ የአሜሪካ መንግሥት ዜጎቹን ከሶማልያ በአፋጣኝ ሲያስወጣ በእግሩ የኢትዮጵያ ሰራዊት እንዲተካ ከአሜሪካ መንግስት ትእዛዝ የተቀበለው የወቅቱ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር የአገሪቱን ሠራዊት ከምክር ቤታችን እውቅና ውጪ እንዲዘምት አድርገዋል።

አሁንም የፕሬዚዳንት ባይደን ጥረት አሸባሪውን ህወሃት መልሶ በመንበሩ በማስቀመጥ በራስ መተማመን እና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን የዘወትር ተረጂ ማድረግ ሲሆን፣ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ደግሞ ከእንግዲህ ይህ ጨርሶ የማይታሰብ ቅዠት ነው።

ከዚህ ተግባር በባሰ መልኩ በማር የተለወሰ መርዛምነት ያለውን ተግባር የፈፀመው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሃፊ አንቶንዮ ጉተሬዝ ለተነሱ ጥያቄዎች የሰጡት ምላሽ የመሟገቻ አነጋገር ነው።"... ከኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ተነጋግረናል፣ ከዶክተር ደብረጽዮንም ደብዳቤ ደርሶኛል እኔም ጉዳዩን እንዲያጣራ ወኪል ልኬያለሁ" ብለዋል።

ይሄ ነው ገራሚው ድርጊት። ዶክተር አቢይ በህጋዊ መንገድ ሕዝብ የመረጣቸው የሉዓላዊት ኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ፣ ደብረፅዮን ደግሞ ለሕግ አልገዛም ብሎ ያመፀና ወደ ሽፍትነትና የዞረና በኢትዮጵያ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀ ነው።ይህ ሆኖ ሳለ እንደ መንግሥታቱ አባል ተቆጥሮ በዋና ፀሃፊው ደብዳቤውን መቀበልና፣ ይባስ ብሎ ወኪል ልኬያለሁ ማለታቸው የመንግሥታቱን ደንብና ስርዐት የጣሰ አካሄድ ነው።

ዋና ፀሃፊ ለምን ይህን ስህተት፣ ስህተት መሆኑን እያወቁ ፈፀሙት የሚል ጥያቄ ቢነሳ መልሱ ቀላል ነው። ይህን አሁን ዋና ፀሃፊው የተገበሩትን ስህተት እንዲያደርጉ ያስገደዳቸው የባይደንና የአውሮፓ አገሮች አሸባሪውን ቡን ወደ ሥልጣኑ ለመመልስ (ፍቺ የሌለው ቅዠት ነው) ባላቸው ፍላጎት ላይ የተመሰረተ መሆኑ አያጠራጥርም።

ይህ ባይሆን ኖሮ ጉተሬዝ ደብዳቤውንም አይቀበሉም ወኪልም አይልኩም ነበር።መቼም በጉተሬዝ የሚላኩት ወኪል ወደ ትግራይ ለማቅናት የሚሞክሩት በቦሌ በመሆኑ ወደመጡበት እንጂ መቀሌን እንደማይረግጧት እርግጠኛ ነኝ።

በአንዲት ሉዓላዊት ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትን የመንግሥታቱ ድርጅት ህገ ደንብ አይፈቅድምና እሳቸውም ሆኑ ሌሎቹ "ከሉአላዊትና የመንግሥታቱ ህብረት ቀደምት መስራች አባል ኢትዮጵያ ላይ እጃቸውን ያንሱ"ኢትዮጵያችን የተሰነዘረባትን ጦርነት ድል በማድረግ ወደ ከፍታዋ ትመለሳለች።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም