ቀጥታ፡

ለሀገራችን ህልውና ስንል ያፈሰስነው ደም አይቆጨንም- ጉዳት የደረሰባቸው የሠራዊቱ አባላት

ደሴ፤ መስከረም 18/2014 (ኢዜአ ) የኢትዮጵያን ህልውና ለማስቀጠል በተደረገው ዘመቻ ያፈሰስነው ደማችን አይቆጨንም ሲሉ አሸባሪውን የህወሃት ቡድን ሲፋለሙ ጉዳት የደረሰባቸው የሠራዊቱ አባላት አስታወቁ።

አስር አለቃ ምን አለ በሽር ወደ ሀገር መከላከያ ሠራዊት ተቀላቅሎ  ሀገሩን እና ህዝቡን ለ12 ዓመታት በቅንነትና በታማኝነት አገልግሏል።

በነበረው ቆይታም በሚችለው አቅም ሀገሩን በማገልገሉ የሚሰማው ደስታና ኩራት ወደር እንደሌለው ይናገራል፡፡

በተሰማራባቸው የተለያዩ ግዳጆች ህዝብና መንግስት የጣላበትን ግዳጅ በድል መወጣቱን ጠቁሞ፤ አሁን ደግሞ አሸባሪው የህወሃት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የጀመረውን እኩይ ተግባር  ለማስቆም በተደረገው የህልውና ዘመቻ በወሎ ግንባር በመሰለፍ የድርሻውን መወጣቱን ገልጿል።

''የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ በከፈልኩት መስዋትነት ደሜ ቢፈስም አይቆጨኝም'' ያለው አስር አለቃ ምንአለ፤ በተደረገለት ህክምና እያገገመ በመሆኑ ዳግም ወደ ትግሉ ጎራ በመቀላለቀል የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ ጽኑ ፍላጎት አለው።

ቡድኑ ታይቶ የማይታወቅ አሳፋሪ ተግባር መፈጸሙን የጠቆመው አስር አለቃ ምናለ ፤ ''አንድነታችን ጠብቀን በመደምሰስ  ወደ ልማታችን የምንመለስበት ጊዜ እሩቅ እንደማይሆንም እምነቴ ነው'' ሲል አስታውቋል።

ሌላው የሠራዊቱ አባል ወታደር ማህሪ ዘመን በበኩሉ'' በአባቶቻን አጥንትና ደም ታፍራ፣ ተከብራና ለአፍሪካ ኩራት የሆነችውን ኢትዮጵያን ከእነ ሙሉ ክብሯ ለማስቀጠል የማልከፍለው መስዋትነት የለም'' ብሏል፡፡

ቀደም ሲል በሰሜን ሸዋ  መንዝ አካባቢ በሚሊሻነት  ማገልገሉን አስታውሶ፤ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮጵያን ከጠላት ለመጠበቅ ወደ መከላከያ ሠራዊት መቀላቀሉን ገልጿል፡፡

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ባለፉት 27 ዓመታት በሀገርና በህዝብ ላይ የፈጸመው ግፍና በደል አልበቃ ብሎ  ከውጭ ጠላት ጋር ወግኖ ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰራ መሆኑ ቁጨት እንዳሳደረበት ተናግሯል።

የህወሓትን የሽብር ቡድን እኩይ ሴራ  ለማክሸፍ  በግንባር በመሰለፍ የድርሻውን ሲወጣ መቆየቱን አስረድቷል።

''ለምወዳት እናት ሀገሬ በከፈልኩት ትንሹ መስዋትነት ደሜ ቢፈስም፤ አካል ቢጎዳም አይቆጨኝም'' ያለው ወታደር ማህሪ፤ ከጉዳቱ አገግሞ ቡድኑን ለመደምሰስ እየተደረገ ባለው ዘመቻ ዳግም ለመሳተፍ  ፅኑ ፍላጎት  እንዳለው አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ ያለው አንድነትና ሁለተናዊ ድጋፍ ለሠራዊቱ ወኔ፣ ብርታት አስተዋጽኦ እንደሚያበርክት አምልክቶ፤ አሁንም ህብረተሰቡ አንድነቱን ጠብቆ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት  ጠቁሟል።

የሀገሬን ዳር ድንበር ለማስከበር   በከፈልኩት መስዋዕትነት ተደስቻለሁ፤ አገግሜም ህዝቤን ነጻ አወጣለሁ የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ ያለው ደግሞ  የ61ኛ ክፍለ ጦር አባል ወታደር መሐመድ ሁሴን ነው፡፡

በወሎ ግንባር በመሰለፍ ግዳጁን እየተወጣ ባለበት ወቅት ጉዳት እንደረሰበት ጠቅሶ፤  በጥሩ ጤንነት ላይ በመሆኑ ዳግም ወደ ግንባር በመሰለፍ የሽብር ቡድኑን ለመደምሰስ በሚደረገው ዘመቻ የበኩሉን እንደሚወጣ ገልጿል።

ወጣቱ ወደ መከላከያ ሠራዊቱ በመቀላቀል የሀገሩን ሉዓላዊነት  ማስጠበቅ ይኖርበታል ሲልም መልዕክት አስተላልፏል።

የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴን  ጨምሮ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ሃላፊዎችና ባለድርሻ አካላት በደሴ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በመገኘት አሸባሪው የህወሓት ቡድን ሲፋለሙ ጉዳት ደርሶባቸው በህክምና ላይ ያሉ የፀጥታ አባላትን በመጠየቅ ማበረታታቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም