አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኅብረተሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች ምላሽ ሊሰጥ ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለኅብረተሰቡ አንገብጋቢ ችግሮች ምላሽ ሊሰጥ ይገባል
አዲስ አበባ፣ መስከረም 18/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አዲሱ አስተዳደር ለመዲናዋ ነዋሪዎች ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት ይጠበቅበታል ሲሉ በምስረታ ስነ ስርዓቱ ላይ የታደሙ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ተናገሩ።
ሶስተኛው የመዲናዋ ምክር ቤት "አዲስ ምዕራፍ" በሚል ዛሬ ተመስርቷል።
ለኢዜአ አስተያየታቸውን የሰጡ የሃይማኖት አባቶች፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች አባላትና የኪነ ጥበብ ባለሙያዎች አዲሱ የከተማዋ አስተዳደር ለህብረተሰቡ ጥያቄዎች ምላሽ እንደሚሰጥ ተስፋ ሰንቀዋል።
በከተማዋ አሉ ያሏቸውን የኑሮ ውድነት፣ የትራንሰፖርት፣ የመኖሪያ ቤት እና ሌሎችም ችግሮች ለመፍታት መስራት ይኖርበታል ብለዋል።
ሕዝቡ በነቂስ ወጥቶ መንግስቱን መርጧል፤ የተመረጠው መንግስትም ህዝቡን ዝቅ ብሎ ማገልገልና የገባውን ቃል መፈጸም ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል።
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን መልዓከ ህይወት ቆሞስ አባ ወልደየስ በአዲስ አበባ ከተማ ያለውን የዋጋ ንረት ከተማ አስተዳደሩ በአጭር ጊዜ ተናቦ ፈትቶ የዋጋ ማሰተካከያ አድርጎ ለህብረተሰቡ መልስ ሊሰጥ እንደሚገባ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ዴሞክራቲክ ኅብረት ሊቀመንበር አቶ ገብሩ በርሄ በበኩላቸው "ምክር ቤት ካለፈው ምክር ቤት የተሻለ ሆኖ እንዲገኝ እንጠብቃለን። ምክንያቱም በአዲስ አበባ የኑሮ ውድነት የትራንሰፖርት ፣ የጸጥታ ችግሮችም አሉ፣ የስራ እጥነት ችግር አለ፣ እነዚህን ሙሉ በሙሉ እንኳን ባይሆን በተወሰነ መልኩ ጥሩ ማሳያና ችግር ፈቺ የሆነ እንቅስቃሴ ያደርጋል ብለን ተስፋ እናደርጋለን" ብለዋል።
"ምክር ቤቱ በሰው ስብዕና ፣ፍትሃዊነት ፣እኩልነት ፣ በትምህርት ፣ በኪነ ጥበብ ላይ በሁሉን አቀፍ አገልግሎት ሰጪ እንዲሆን እፈልጋለሁ።" ሲሉ ፍላጎታቸውን የገለጹት ደግሞ ድምጻዊ መምህሩ ጫሞ ናቸው።
አስተያየት ሰጪዎቹ የከተማው ነዋሪዎችም መንግስት ችግሮችን ለመፍታት በሚያደርገው ጥረት የበኩሉን ድጋፍ ማድረግ ይኖርበታል ሲሉም ተናግረዋል።
ሁሉም በየተሰማራበት የስራ መስክ የሃይማኖት አባቶች በፀሎት፣ ህብረተሰቡ ጠንክሮ በመስራት፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች በሙያቸው፤ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች ለከተማዋ ዕድገት የበኩላቸውን ሊወጡ ይገባል ነው ያሉት።
የመዲናዋ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በበኩላቸው አዲሱ አስተዳደር የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እንደሚሰራ በምክር ቤቱ ምስረታ ላይ ገልጸዋል።