ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ወረራውን በጋራ እንደመከቱ ሁሉ በሰብአዊ እርዳታና መልሶ ማቋቋምም እንዲሳተፉ ጥሪ ቀረበ

ባህር ዳር፤ መስከረም 18/2014(ኢዜአ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ ክልል ላይ የፈጸመውን ወረራ ኢትዮጵያዊያን በአንድነት እንደመከቱ ሁሉ በሰብአዊ እርዳታና መልሶ ማቋቋምም ላይም እንዲሳተፉ የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ጥሪ አቀረቡ።
ሽብርተኛው ህወሓት በክልሉ በፈጸመው  ወረራ ለደረሰው  ሰብአዊና ቁሳዊ  ጉዳት ምላሽ ለመስጠት የተቋቋመው የአስቸኳይ  ጊዜ ምላሽ  ማስተባበሪያ ማዕከል  መነሻ ዕቅድ ላይ በባህርዳር ከተማ ውይይት ተካሂዷል።

ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ ወቅት እንዳሉት ፤  አሸባሪው ህ ወሓት ወረራ  ያካሄደበት ዋነኛ ምክንያት  ኢትዮጵያን በማፈራረስ የራሱን የፖለቲካ ግብና ጥቅም ለማሳካት ነው።

ሴራውን የተገነዘበው የኢትዮጵያ ህዝብም የጥፋት ቡድኑ  እያካሄደ  ያለውን ወረራ በአንድነት በመቆም እየመከተ መሆኑን ተናግረዋል።

በወራሪው በአሸባሪው ህወሓት በርካታ ንጹሃን ዜጎች ከመገደላቸው ባለፈ ሃብትና  ንብረታቸው መዘረፉንና ከቄያቸው መፈናቀላቸውን የጠቆሙት ዶክተር ፋንታ፤ ችግሩን ለመቋቋም የእለት ምግብ፣ መድሃኒትና የውሃ አገልግሎቶችን ተደራሽ ማድረግ እንደሚገባ አመልክተዋል።

ኢትዮጵያዊያን በጋራ ቆመው ጦርነቱን እንደመከቱ ሁሉ የተፈናቀሉ ዜጎችን ወደነበሩበት አካባቢ በመመለስ እንዲቋቋሙ ለማድረግ በሚሰራው ስራም የበኩላቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ተፈናቃዮቹን እንዲቋቋሙ የማስተባበሪያ ማዕከል ተቋቁሞ ወደ ሥራ መግባቱን ገልጸው፤ የፌደራል ተቋማት፣ ረጂ ድርጅቶችና መላ ህዝቡ ከማዕከሉ ጋር በትብብር እንዲሰሩም  ጥሪ አቅርበዋል።

"አሸባሪው ቡድን በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች መጠነ ሰፊ ችግር አስከትሏል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል አደጋ መከላከል፣ ምግብ ዋስትናና  ልዩ ድጋፍ  የሚሹ  አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽነር ዘላለም ልጃለም ናቸው።

በችግር ውስጥ ላሉ ዜጎች የምግብ፣ የመድሃኒት፣ የውሃና ሌሎች ሰብአዊ ድጋፎችን ተደራሽ ለማድረግ የሚመለከታቸው ተቋማትንና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን ያካተተ የማስተባበሪያ ማዕከል መቋቋሙን አስታውቀዋል።

ጠላት አሁንም በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች የሚገኘው ህዝብ በረሃብ ከማለቁ በፊት የማዕከሉ አባላት የሆኑ የዓለምአቀፍ   ግብረ ሰናይ  ድርጅቶች  ምግብና መድሃኒት  እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል።

ማዕከሉ ተንቀሳቃሽ  የድጋፍ ስርዓት  በመዘርጋት ከወረራ  ነጻ የሚወጡ አካባቢዎችን  ፈጥኖ በመድረስና ነጻ ባልወጡ አካባቢዎች ያሉ ዜጎችም በአዋሳኝ ወረዳዎች ድጋፍ የሚያገኙበት ሁኔታ ማመቻቸት እንዳለበት አመልክተዋል

"ማዕከሉ በሚያስቀምጠው  አቅጣጫ መሰረት  የረጂ ድርጅቶች  ሃብትን፣  እውቀትንና  ልምድን  ማስተባበር ያስፈልጋል" ያሉት ደግሞ የአሜሪካን የደን  አገልግሎትና  የአደጋ ሥራ አመራር ቴክኒካል ስፔሻሊስት ወይዘሮ ራሄል አስፋ ናቸው።

በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮች የሚደረገው ድጋፍ እንዳይደጋገምና ፍትሃዊነትን ለማረጋገጥ ሲባል ማዕከሉ በሚሰጠው አቅጣጫ መስራት እንደሚገባም አመልክተዋል።

በብሔራዊ የአደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አማካሪ አቶ ሙሉነህ ወልደማርያም በበኩላቸው፤ "ማዕከሉ ውጤታማ እንዲሆን ሰባት የሥራ ቀጠናዎች ተለይተዋል" ነው ያሉት።

እነዚህም ምግብ፣ ጤና፣ ውሃ፣ መጠለያ፣ ትምህርት፣ ግብርና እና ከምግብ ውጭ  በሚል በሰባት ቀጠና ተለይተው  የሚከናወኑ ተግባራት መሆናቸውን አስረድተዋል።

አማካሪው እንዳሉት፤ ማዕከሉ ሁሉንም ተግባራት በራሱ መተግበር ስለማይችል በማዕከሉ የታቀፉ ተቋማት እቅዱን ከራሳቸው ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ወደ መሬት ማውረድ ይጠበቅባቸዋል።

"ይህም ስራውን ወደ ዞንና  ወረዳ በማውረድ   ከዕለት ምግብ  ድጋፍ እስከ መልሶ  ማቋቋም ተግባራትን በሙሉ ሃላፊነት እንዲፈጽሙ ያግዛል" ብለዋል።

በአማራ ክልል አሸባሪው ህወሓት በፈጸመው ወረራ ከ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ህዝብ በላይ በችግር ውስጥ እንደሚገኝ የኢዜአ ሪፖርተር ከባህርዳር ዘግቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም