የተፎካካሪ ፓርዎች አመራር አባላት አቶ ግርማ ሰይፉና አቶ የሱፍ ኢብራሂም የካቢኔ አባል ሆኑ - ኢዜአ አማርኛ
የተፎካካሪ ፓርዎች አመራር አባላት አቶ ግርማ ሰይፉና አቶ የሱፍ ኢብራሂም የካቢኔ አባል ሆኑ
አዲስ አበባ መስከረም 18/2014 (ኢዜአ) የተፎካካሪ ፓርቲ አመራር አባላት የሆኑት አቶ ግርማ ሰይፉና የሱፍ ኢብራሂም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የካቢኔ አባል ሆነው ተመረጡ።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት ምስረታ ስነ-ስርዓት ዛሬ በከተማ አስተዳደሩ ማዘጋጃ ቤት እየተካሄደ ይገኛል።
በዚሁ ስነ-ስርዓት ላይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ የካቢኔ አባላት ሹመት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።
ከንቲባዋ ለካቢኔ አባላት ሹመት ካቀረቧቸው እጩዎች መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ፓርቲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ግርማ ሰይፉ እና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) ፓርቲ ምክትል ሊቀመንበር አቶ የሱፍ ኢብራሂም ይገኙበታል።
አቶ ግርማ ሰይፉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር፤ አቶ የሱፍ ኢብራሂም የመንግስት ንብረት አስተደዳር ባለስልጣን ሃላፊ ሆነው እንዲመሩ ለምክር ቤቱ ቀርበዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ ብልጽግና ፓርቲ ስድስተኛ አጠቃላይ ምርጫ ካሸነፈ የተፎካካሪ ፓርቲዎች በመንግስት ተቋማት ውስጥ ሃላፊ ሆነው እንዲሾሙ ቃል መግባቱን አስታውሰዋል።
ቃል በተገባው መሰረት የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲዎች አመራር አባላት በካቢኔ ውስጥ እንዲካተቱ መደረጉንና "ይሄም አዲስ የፖለቲካ ልምምድ መፍጠርን ዓላማ ያደረገ ነው" ብለዋል።
የአዲስ አበባ ምክር ቤት የቀረበለትን የካቢኔ አባላት ሹመት በ120 ድጋፍ በአንድ ተቃውሞና በአራት ድምጸ ተአቅቦ በአብላጫ ድምጽ አጽድቆታል።
በዚሁ መሰረት አቶ ግርማ ሰይፉ የኢንቨስትመንት ኮሚሽነር እንዲሁም አቶ የሱፍ ኢብራሂም መንግስት ንብረት አስተደዳር ባለስልጣን ሃላፊ ሆነዋል።
የተሾሙት የካቢኔ አባላት ሕዝብ የሰጣቸውን ሃላፊነት በታማኝነትና በቅንነት ለማገልገል ቃል በመግባት ቃለ መሐላ ፈጽመዋል።