ቀጥታ፡

የምእራቡ ዓለም ያልተገባ ተጽእኖ

ሰሞኑን የተደረገው 76ኛው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ የሀገራት መሪዎች ከወትሮው ለየት ባለ መልኩ በውጭ ጣልቃ ገብነት ላይ ትኩረት አድርገው ጠንካራ መልእክቶችን አሰተላልፈዋል። የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሰይድ ኢብራሂም የምእራቡን ዓለም ያልተገባ ጣልቃ ገብነት ካወገዙት መካከል አንዱ ናቸው።

ፕሬዝዳንቱ በንግግራቸው ኢራን ፍትሓዊ ባልሆነ መንገድ የተጣለባት የአሜሪካ ማዕቀብ ሊያበቃ እንደሚገባ አሳስበዋል። ከዚሁ ጋር አያይዘው እጅ የማስረዘምና ምክንያታዊነት በሌለው አካሄድ ሕዝብን መጫን ተቀባይነት የሌለው ነው ሲሉ ተችተዋል፡፡

የቻይናው ፕሬዝዳንት ሺ ዥን ፒንግ በበኩላቸው ዴሞክራሲ ሁሉም አገራት እንዲቀዳጁት የሚጠበቅ እንጂ ለአንድ አገር ብቻ የተሰጠ ልዩ መብት አይደለም በማለት የምእራቡን ዓለም ያልተገባ አካሄድ ተችተዋል፡፡ እንደ ሩሲያ፣ ቱርክ፣ ህንድ እና በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች በንግግራቸው የምእራቡ ዓለም ያልተገባ ጫና ተቃውመዋል።

በዚሁ ጉባኤ ላይ ሃገራቸው ኢትዮጵያን ወክለው የተገኙት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረጉ ሙከራዎች ተቀባይነት የሌላቸው ስለመሆናቸው አስምረው ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት የሰብአዊ እርዳታን በተመለከተ ያልተቆጠበ ቁርጠኝነት እንዳለው አመልክተው፤ ነገር ግን የትኛውንም ጣልቃ ገብነት ኢትዮጵያ እንደማትቀበል አስረድተዋል።

አቶ ደመቀ መኮንን በዚሁ ንግግራቸው ላይ አጽንኦት ከሰጡት ጉዳይ አንዱ በትግራይ ክልል ከተፈጠረው ቀውስ ጋር በተያያዘ የምእራቡ ዓለም የሰብአዊ እርዳታን ለፖለቲካ ዓላማ እያዋለ ስለመሆኑ ነው። ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ “አሁን በደረስንበት ምዕራፍ የሰብአዊ ድጋፍ የፖለቲካ ዓላማን ማስፈፀሚያ መሳሪያ እንደሆነ እየተገነዘብን ነው” በማለት ነበር የገለጹት። በትግራይ ክልል አሸባሪው ቡድን የሐሰት መረጃን በማቀነባበር የተዛባ ግንዛቤ እንዲፈጠር ማድረጉን በመጠቆም በዚህም የምእራቡ ዓለም ሐሰተኛ ውንጀላ ማቅረቡን ተናግረዋል።

በትግራይ ክልል ውስጥ የተቀሰቀሰውን ጦርነት ተከትሎ ምዕራባውያን በተለይ አሜሪካ እና አንዳንድ የአውሮፓ ህብረት አባል አገራት በመንግስት ላይ በተለየ መልኩ ጫና ለማሳደር ጥረት ሲያደርጉ መሰንበታቸው የሚታወቅ ነው። የቅርቡን እንኳ ቢወሰድ የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የተለያዩ ማዕቀቦችን ለመጣል የሚያስችል ትዕዛዝ ላይ ፊርማቸውን አኑረዋል።

በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል ከተቀሰቀሰው ጦርነት ጋር በተያያዘ አንዳንድ ምእራባውያን አገራት፣ ድርጅቶችና ግለሰቦች አሸባሪው ህወሓት የሚፈጽማቸው ኢሰብአዊ ጭፍጨፋዎች፣ የንብረት ዝርፊያና ውድመት አይተው እንዳላዩ ማለፋቸው ብዙዎችን ያስገረመ ሆኗል። የሽብር ቡድኑ በአገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ስለፈጸመው ጥቃት ከማውገዝ ይልቅ እንደተበዳይ ሲሟገቱለት ተስተውሏል። ይልቁንም ተጨባጭ ያልሆኑ የፕሮፖጋንዳ መረጃዎች ጭምር በማደራጀት ተፈጸመዋል የተባሉ ጥፋቶች በሙሉ መንግስትን ተጠያቂ በማድረግ ያልተገባ ጫና ሲያሳድሩ ቆይተዋል።

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን ለማተራመስ በነደፈው እቅድ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች የፈጸመው ወረራ  ቡድኑ ማንነቱን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ፍንትው አድርጎ ያሳየ ነው። ይሁን እንጂ ድርጊቱን ከማውገዝና እንዲቆጠብ ከማስጠንቀቅ ይልቅ በጦርነቱ አሸናፊ እንደሚሆን በጉጉት ሲጠባበቁ ነበር። ምእራባውያን መገናኛ ብዙሃኖችም የሽብር ቡድኑን ወረራ በሰበር ዜናነት ሽፋን እየሰጡ በአጭር ጊዜ አዲስ አበባን እንደሚቆጣጠር ሲያስተጋቡ እንደነበር የሚታወስ ነው።

ለአሸባሪው ህወሃት ሁሉን አቀፍ ድጋፍ የማድረግ ፍላጎት እንዳላቸው ግልጽ ያደረጉት ምእራባውያኑና ተቋሞቻቸው የሰብአዊ እርዳታ ስርጭትን ምክንያት አድርገው የኢትዮጵያን ህዝብና መንግስት ስም ለማጠልሸት የተቀናጀና የተደራጀ ዘመቻ የጀመሩት ገና ከማለዳው አሸባሪው ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከሰነዘረበት ማግስት ጀምሮ ነበር። ይህን ተከትሎ በርካታ ሃሰተኛ ዘገባዎች በመፈብረክ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሰራጭተዋል፤ አሁንም በማሰራጨት ላይ ናቸው።

እነዚሁ መንግስታትና ድርጅቶቻቸው መንግስት ሲወስዳቸው የነበሩ በጎ እርምጃዎችን ከምንም ባለመቁጠርና የወንጅሉን ፈጻሚዎች ተጎጂ አድርጎ የመሳል ስራ ላይ ተጠምደው ከመክረማቸውም በላይ አሸባሪ ድርጅቱ ፖለቲካም ሆነ ወታደራዊ እንቅስቃሴው ላይ ምንም ድርሻ ያልነበራቸውን ንጹሃንን በማይካድራ፣ በጋሊኮማ፣ በጭና በቆቦና በሌሎች ቦታዎች በጅምላ ፈጅቶ አስከሬናቸውን ሲጥል ምንም ለማለት አልፈለጉም።

የህግ ማስከበር ዘመቻውን ተከትሎ ለሁሉም የትግራይ ክልል ህዝብ በሚያስብል ደረጃ አብዛኛውን ሰብአዊ እርዳታና የነዳጅ አቅርቦት የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት ሲያቀርቡ እንደነበር እየታወቀ “ሰብአዊ እርዳታ ለማዳረስ መንገዶች ሁሉ ተዘግተዋል” ሲሉ የከረሙት ምእራባውያን መንግስታት፣ የሚዲያ ድርጅቶቻቸውና ግለሰብ ተንታኞች አሁንም የበፊቱ ጩኸት ላይ ናቸው። እነዚህ አካላት በእርግጥ ለሰብአዊነት ተቆርቋሪ ቢሆኑ ኑሮ በአማራና በአፋር ክልል ስለተፈናቀሉ ሰዎች እኩል ድምጽ ማሰማት በቻሉ ነበር። አሸባሪው ድርጅት በአፋርና በአማራ ክልሎች በሺዎች የሚቆጠሩ ንጹሃንን በመግደልና ቁስለኛ በማድረግ ሚሊዮኖችን አፈናቅሎ ሃብትና ንብረታቸውን በመዝረፍና እንዳይጠገኑ አድርጎ ሲያወድም ድምጻቸውን ለማሰማት አለመፍቀዳቸው ጥያቄ ማስነሳት ጀምሯል።

የአሸባሪ ድርጅቱን አላማ ለማሳካት እንዲያግዛቸው የሰብአዊ እርዳታ ስርጭትን ከተገቢው በላይ በማስጮህ የአለምን ትኩረት የሳቡት እነዚሁ አካላት እርዳታን በሚመለከት ነጻናት ፍትሃዊነት ገለልተኝነትና አለማዳላትና የመሳሰሉትን አለምአቀፍ የቃልኪዳን መርሆዎች ችላ በማለት አሸባሪው ከአፋርና ከአማራ ክልል ላፈናቀላቸው ንጹሃን ተጎጂዎች ድጋፍ እያደረጉ አይደለም። በተመሳሳይም የሚዲያ ተቋሞቻቸው በተከፋይ ምሁራንና ተንታኞቻቸው በኩል ሚያቀርቧቸው የሚዲያ ስራዎች ከመሰረታዊ የጋዜጠኝነት ሙያዊ መርሆዎች በእጅጉ የራቁ ሲሆኑ አብዛኞቹ ዘገባዎችም ውንጀላዎችና የማጠልሸት ተግባራትን ዋነኛ ግብ አድርገው ለመሰራታቸው በርካታ  አብነቶችን ማንሳት ይቻላል።

የምእራቡ ዓለም ያልተገባ ጣልቃ ገብነትና ጫና አሁንም ቀጥሏል። ምንም እንኳ እውነታው በሂደት እየተገለጠ ሲመጣ አሁን ከያዙት አቋም ለውጥ ያሳዩ ይሆናል የሚል ግምት ቢኖርም ጫናውን ለመቋቋም ኢትዮጵያውያን በአንድነት መቆም ከምንም በላይ ወሳኝ የሆነ ምእራፍ ላይ እንገኛለን። ዛሬ ለሃገር መቆም ካልተቻለ ለነገ መቆሚያ ሃገር ስለሚያሳጣ እነዚህ አካላት የሚያራግቡትን ሀገር የማፍረስ አጀንዳ በዝምታ መመልከት አስፈላጊ ባለመሆኑ ኢትዮጵያውያን ከጫፍ እስከጫፍ ሁሉንም አይነት መስዋእትነት ለመክፈል መትመማቸውን ቀጥለዋል።   

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም