ቀጥታ፡

በህዝብ ትክክለኛ ድምፅ መንግስት መመስረት የተቻለበት ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጥሯል

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ ህዝብ ትክክለኛ ድምፅ መንግስት መመስረት የተቻለበት ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጥሯል ሲሉ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ ምሁር ተናገሩ።

መንግስት ለህዝቡ የገባውን ቃል ለመፈፀም  በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባልም ብለዋል።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ሶሻል አንትሮፖሎጂ ትምህርት ክፍል ረዳት ፕሮፌሰር ዶክተር ተካልኝ አያሌው ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት ኢትዮጵያ በውስጥና በውጭ ያጋጠሟትን ፈተናዎች ተጋፍጣ በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነት ያለው ሰላማዊ ምርጫ በማካሄድ ስኬታማ ሆናለች።

ኢትዮጵያዊያን የአገር ህልውና እና ሉዓላዊነት ለማንም ቢሆን አሳልፈው እንደማይሰጡና የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው መወሰን መቻላቸውን በነቂስ ወጥተው በመምረጥ በተግባር ማሳየታቸውንም ጠቅሰዋል።

"የኢትዮጵያ መሪዎች ስልጣንን በአፈሙዝ ሲቆናጠጡ ነበር" ያሉት ዶክተር ተካልኝ በኢትዮጵያ በህዝብ ትክክለኛ ድምፅ መንግስት መመስረት የተቻለበት ታሪካዊ አጋጣሚ ተፈጥሯል ብለዋል።

በህዝቦች ይሁንታ ወደ ማስተዳደር የመጣው አዲስ መንግስት በርካታ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና የኢኮኖሚ ክንውኖች ይጠብቁታል ነው ያሉት።

ኢትዮጵያ በ6ኛው ዙር ያካሄደችው ጠቅላላ ምርጫ እኩይ አላማ ላነገቡ አንዳንድ አገራት ጥሩ ምላሽ የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

የራሳችንን ጉዳይ በራሳችን መወሰን፤ በአገር ሉዓላዊነት ጉዳይ ማንም ጣልቃ ሊገባ አይችልም የሚሉና ሌሎችንም መልዕክቶች ያስተላለፈ ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት በህዝብ ትግል ለውጥ መምጣቱን ተከትሎ በርካታ ፈተናዎችና መልካም አጋጣሚዎች መከሰታቸው ይታወሳል።

በለውጡ ዓመታት ኢትዮጵያ ባጋጠማት የውስጥና የውጭ ችግሮች በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ተከስተው የሰው ህይወት ጠፍቷል፣ ንብረት ወድሟል፣ በርካታ መፈናቅሎችም አጋጥመዋል።

በሌላ በኩል ደግሞ አደጋ ውስጥ ገብቶ የነበረው የኢትዮጵያዊነትና የአገር ፍቅር ስሜት ያንሰራራ ሲሆን ከውስጥና ከውጭ የሚያጋጥሙ ፈተናዎችን ዜጎች በጋራ ለመመከት አንድነታቸውን አጠናክረዋል።

የኢትዮጵያ የልማት ተስፋ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ መፋጠንና የመጀመሪያና ሁለተኛ ዙር ውሃ ሙሌት በታቀደው የጊዜ ሰሌዳ መከናወኑ በስኬት ተመዝግቧል።

6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ በሰላማዊ መንገድ መካሄድ እንዲሁም ትላልቅ አገራዊ የልማት ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ከተመዘገቡ ስኬቶች መካከል ይጠቀሳሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም