ቀጥታ፡

"ከመጋቢት እስከ መጋቢት"

አዲስ አበባ፣ መስከረም 18/2014 (ኢዜአ) የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድን መልዕክቶች የያዘ "ከመጋቢት እስከ መጋቢት" የተሰኘ መጽሃፍ ለንባብ በቅቷል።
መጽሃፉ በሶስት ጥራዞች የተዘጋጀ ሲሆን፤ ከታሪካዊው የጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የመጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም የፓርላማ ንግግር እስከ 125ኛው ዓመት የአድዋ ድል በዓል መልዕክቶች ተሰንደውበታል።

በመጽሃፉ የተካተቱ ከ176 በላይ መልዕክቶች፣ ንግግሮችና መግለጫዎች በአማርኛ፣ በአፋን ኦሮሞ፣ በትግሪኛና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች የተደረጉ ናቸው።

በጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት ፕሬስ ሴክሬታሪያት የተዘጋጀው ይህ መፅሃፍ ዛሬ ለንባብ በቅቷል።

ከመጽሃፉ ሽያጭ የሚገኘው ገቢ በአሸባሪው የህወሓት ወረራ ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ ወገኖች እንደሚውል በመጽሃፉ የምረቃ ስነ-ስርዓት ላይ ተገልጿል።

በምረቃው ላይ የመጽሃፉን መልዕክቶች ተግባቦታዊ፣ ፓለቲካዊና ዲፕሎማሲያዊ እንዲሁም ኢኮኖሚያዊ አቀራብ የተመለከተ ዳሰሳ ቀርቧል።

መሪዎች ራዕያቸውንና ዓላማቸውን ለሕዝብ በሚገባ ማስተዋወቅ አለባቸው ያሉት የጋዜጠኝነትና ኮሙኒኬሽን ባለሙያ አቶ ነጻነት ተስፋዬ፤ ይህም በመሪዎችና በሕዝብ መካከል ተቀራርቦና ተናቦ መስራትን ይፈጥራል ብለዋል።

ዓላማና ራዕይን በዙሪያ ላሉ ሰዎች ብቻ ማስተዋወቅ የሚፈለገውን ውጤት እንደማያመጣም ጠቁመዋል።

ከዚህ አኳያ የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክቶች "እርሳቸው ማን እንደሆኑና ለሕዝብ ምን እንደሚያስቡ ተግባቦትን የፈጠሩ ናቸው" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ ወደ ሃላፊነት ሲመጡ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ለኢትዮጵያ ያላቸው ራዕይ በሕዝብ ዘንድ በቀላሉ ሊታወቅ መቻሉን ለአብነት አንስተዋል።

በሚኒስትር ማዕረግ የዴሞክራሲ ማዕከል አስተባባሪ ዶክተር ቢቂላ ሁሪሳ በበኩላቸው የጠቅላይ ሚኒስትሩ መልዕክቶች የኢትዮጵያን የፖለቲካ ድባብ የቀየሩ መሆናቸውን አንስተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ንግግራቸውን የፖለቲካ መልዕክቶች ከሚታወቁበት ደረቅ አቀራረብ ይልቅ ቀለል ባለና ማኅበረሰቡ አካባቢውን በመመልከት እንዲገነዘባቸው በሚያደርግ አግባብ በማቅረብ አዲስ አካሄድ ማሳየታቸውንም ተናግረዋል።

መልዕክቶቹ የማኅበረሰብን እውቀት የተዋሱ መሆናቸውን ጠቅሰው፤ ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል በሚያካትት መልኩ መቅረባቸውን አብራርተዋል።

መልዕክቶቹ በዋናነት የተቋም ግንባታ፣ ወንድማማችነት፣ ዘላቂ ሠላም፣ የአገር ግንባታ፣ የዜጎች ክብር፣ ቀጣናዊ ትስስርና ሌሎች አንኳር ጉዳዮች ላይ ያተኮሩ መሆናቸውንም ዶክተር ቢቂላ አውስተዋል።

"የጠቅላይ ሚኒስትሩን መልዕክቶች መልስ ብለን ብንመለከት አንድ ነገር ላይ እርግጠኛ እንሆናለን፤ እርሱም የኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ስብራት ከኢትዮጵያዊያን አቅም በላይ እንዳልሆነ እንደሚያምኑ ነው" ያሉት ደግሞ የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ኢዮብ ተካልኝ ናቸው።

በተለይ በተለያዩ የአገሪቷ አካባቢዎች ተንቀሳቅሰው ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ኢትዮጵያ እምቅ የተፈጥሮ ሃብት ባለቤት መሆኗን አጽንኦት ሰጥተው እንደተናገሩም ነው የገለጹት።

መልዕክቶቹ ዓይናችንን ከፍተን በዙሪያችን ያለውን የተረሳ ሃብት እንድንመለከት ያደረጉ ናቸው ያሉት ሚኒስትር ዴኤታው፤ የገበታ ለሸገር ፕሮጀክት የዚሁ መልዕክት ፍሬ መሆኑን አብራርተዋል።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የመዕሃፉ ምረቃ ስነ-ስርዓት ታዳሚዎች፤ መጽሃፉ ኢትዮጵያ ባለፉት ሶስት ዓመታት ከየት ተነስታ የት እንደደረሰች መመርመር እንደሚያስችል ገልጸዋል።

በተለይ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪዎች ለውጡን በሚመለከት ለሚያደርጉት የምርምር ስራ በግብዓትነት ሊጠቀሙት እንደሚችሉም ተናግረዋል።

የመጽሃፉ ስነ-ጽሁፋዊ ፋይዳ ጉልህ መሆኑን አንስተው፤ መጽሃፉን በሚመለከት ሰፋ ያለ የግምገማ መድረክ ሊዘጋጅ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም