የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠንን አደራ በላቀ አፈፃፀም ለመወጣት ተዘጋጅተናል - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠንን አደራ በላቀ አፈፃፀም ለመወጣት ተዘጋጅተናል
አዲስ አበባ መስከረም 18/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጠንን አደራ በላቀ አፈፃፀም ለመወጣት ተዘጋጅተናል ሲሉ የአየር ሃይል ከፍተኛ መኮንኖች ተናገሩ።
ከኢዜአ ጋር ቆይታ ያደረጉ የአየር ሃይል ከፍተኛ መኮንኖች አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ሕዝብ የሰጠውን ሃላፊነት ሲወጣ፣ ሰራዊቱ ድግሞ አገሩንና ህዝቡን የመጠበቅ ግዴታውን በአግባቡ ይፈፅማል ብለዋል።
ኮለኔል ፈራጅ ኢዲሪስ ለ27 ዓመታት በኢፌደሪ መከላከያና አየር ሃይል ውስጥ ያገለገሉ አንጋፋ የሰራዊት አባል ናቸው።
የኢትዮጵያ ሕዝብ ነጻ ምርጫ አካሂዶ ይበጀኛል ያለውን መንግስት መምረጥና መሾም ሕገ መንግስታዊ መብት አለው ይላሉ።
አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ደግሞ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰጠውን ሃላፊነትና አደራ መወጣት አለበት ብለዋል።
በሕዝብ የተሾመው መንግስት የሚሰጠውን ግዳጅ መቀበልና ሕዝብን መጠበቅ የሰራዊቱ ዋነኛ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
የአየር ሃይል አባላት የኢትዮጵያ ህዝብ የሰጣቸውን አደራ በላቀ አፈፃፀም ለመወጣት ዝግጁ ናቸው ሲሉ ኮሎኔሉ ገልጸዋል።
በአየር ሃይል ለ30 ዓመት ያገለገሉት ኮለኔል ኦሰበር ጉዶም፤ አዲሱ የሚመሰረተው መንግስት ለኢትዮጵያ ሕዝብ ማድረግ የሚችለውን ሁሉ እንደሚሰራ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
የአየር ሃይል አባላት ደግሞ አገራቸውንና ህዝባቸውን የመጠበቅ ግዴታቸውን በላቀ አፈፃፀም ይወጣሉ ሲሉ ተናግረዋል።
የኦሮሚያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግስት መስከረም 15 ቀን 2014 ዓ.ም የተመሰረተ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤትም በዛሬ እለት ተመስርቷል።
በቀጣይም ሌሎች ክልሎች የመንግስት ምስረታ የሚያካሂዱ ሲሆን መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ደግሞ የፌዴራል መንግስቱ ምስረታ የሚካሄድ ይሆናል።