ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊነት በቀላሉ የማይመረመር አገርና ሕዝብን ከግል ጥቅምና ፍላጎት በላይ የመውደድ መገለጫ ነው

መስከረም 18 ቀን 2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊነት በደምና በአጥንት በአያሌ ትውልዶች መስዋዕትነት የተገነባ ጥልቅና በቀላሉ የማይመረመር አገርንና ሕዝብን ከግል ጥቅምና ፍላጎት በላይ የመውደድ መገለጫ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

አዲሱ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ሲመሰረት ወይዘሮ አዳነች አቤቤን ከንቲባ በማድረግ በሙሉ ድምጽ መርጧቸዋል።

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት "ይህ ቀን የሁላችንም ድል ቀን ነው! የኢትዮጵያ ሃቅ፤ የኢትዮጵያ እውነት፤ የኢትዮጵያ ፍላጎት ያሸነፈበትና እውን የሆነበት፤ ለመላው ዓለም በደማቅና በጉልህ ቋንቋም የተሰማበት ነው" ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በማንነት፣ በባህል፣ በታሪክና በሃይማኖት ህብር የተሞላች ጥንታዊት ባለብዙ ድንቅ እና አኩሪ ታሪክ  ባለቤትና ታላቅ ሃገር መሆኗንም ተናግረዋል፡፡

6ኛው አገራዊ ምርጫ ከአንድ ምርጫ ሂደት በላይ የማንነትና የህልውና ነው በሚል የፀና እምነትና ቁርጠኝነታቸውን ባሳዩ  መላ ኢትዮጵያውያን እውን መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡

"ጠላቶቻችን በአደባባይ ሽንፈት የተከናነቡበትና ከእውነትና ከኢትዮጵያ ጎን ለቆሙ አጋሮቻችንን ደግሞ ኩራት መሆን  የቻልንበት ነው" ሲሉም ተናግረዋል፡፡

በዚህም አገር ወደ አዲስ ቀጣይ ምዕራፍ ያሸጋገርንበት ምርጫ አካሂደናል ብለዋል ከንቲባዋ፡፡

በቀጣይም አዲሱ ካቢኔ የእጦትና የስግብግብነት አካሄድን በማስወገድ እንዲሁም ከሙስና የጸዳ ነፃና ገለልተኛ አካሄድ በመከተል ይሰራል ሲሉ አረጋግጠዋል፡፡

አመራሮቹ ከተማዋንና ነዋሪዎቿን የሚመጥን አገልግሎት እንደሚሰጡ ጠቅሰዋል፡፡

የሕዝቡን አዳጊ የኢኮኖሚ ፍላጎት በማሟላት ወደ ተሻለ ደረጃ እናሳድጋለን፤ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የከተማዋን ነዋሪዎች ከዘላቂ ድህነት ለማውጣት በቁርጠኝነት እንሰራለን ብለዋል፡፡

በከተማዋ ከሚገኙ የንግድ ማኅበረሰብ አባላት ጋር ሀብትና ውጤታማ የሃብት አስተዳደር በመፍጠር ኅብረተሰቡን ተጠቃሚ እናደርጋለንም ነው ያሉት፡፡

ከንቲባዋ የመንግስት ተቋማትን ሪፎርም በፍጥነት በማከናወን ተደራሽነቱን እናሰፋለን ሲሉም ገልጸዋል።

መሰረተ ልማትን ከማስፋፋት ባለፈ በጥራት በመስራት የመኖሪያ ቤት እጥረትን መቅረፍ በልዩ ሁኔታ ይሰራበታል ብለዋል፡፡

የሌብነትና የዝርፊያ አስተሳሰብን ከመሰረቱ ለመቅረፍ የተጠያቂነት አሰራር እንደሚዘረጋም አረጋግጠዋል፡፡

የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ሕገወጥነትን ለመከላከል በትኩረት እንደሚሰራም ጠቅሰዋል፡፡

ጥራቱ የተረጋገጠ የጤናና የትምህርት ተደራሽነት እንደሚዘረጋም ገልጸዋል፡፡

የአረጋዊያንንና አካል ጉዳተኞችን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ፤ አዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የሚያስችሉ ተግባራት በስፋት እንደሚተገበሩም ነው የተናገሩት።

አዲስ አበባን የአፍሪካ የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ ያለመሰልቸት እንደሚሰሩም ገልጸዋል፡፡

በመጨረሻም እምነቱን በመጣል ድምጹን የሰጣቸውን የከተማዋን ነዋሪ በማመስገን በቀጣይም የላቀ ድጋፋችሁ አይለየን ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም