ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ወይዘሮ ቡዜና አልቃድርን አፈ-ጉባኤ አድርጎ መረጠ

መስከረም 18/2014 (ኢዜአ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት ወይዘሮ ቡዜና አልቃድርን አፈ-ጉባኤ አድርጎ በሙሉ ድመፅ መረጠ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳር አዲሱን የመንግስት ምስረታ ስነ-ስርዓት እያካሄደ ይገኛል።

ምክር ቤቱ ወይዘሮ ቡዜና አልቃድርን አፈ-ጉባኤ አድርጎ በሙሉ ድምፅ መርጧል።

ወይዘሮ ቡዜና አልቃድር የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታና የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት አባል የነበሩ  ናቸው።

የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት ዛሬ በሚያካሂደው የአዲስ መንግስት ምስረታ ጉባኤ ከአፈ-ጉባኤ ከመምረጥ በተጨማሪ የተለየያዩ ሹመቶችንም ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል።

አዲሱ ምክር ቤት ሶስተኛው የአዲስ አበባ ምክር ቤት ሲሆን ከዚህ ቀደም የነበረው ምክር ቤት ለስድስት ዓመት ከተማዋን ሲመራ ቆይቷል።

የአዲስ አበባ ምክር ቤት 138 መቀመጫዎች አሉት።

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ምክር ቤት ከተካሄደው ምርጫ በተጨማሪ ለ23 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ ውድድር መደረጉ ይታወቃል።

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው ስድስተኛ አጠቃላይ ምርጫ የተካሄደ ሲሆን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 138 መቀመጫን ለማግኘት 14 የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወዳድረዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሐምሌ 3 ቀን 2013 ዓ.ም ይፋ ባደረገው ውጤት ብልጽግና ፓርቲ የምክር ቤቱን ሁሉንም መቀመጫዎች ማሸነፋን ገልጾ ነበር።

በኢትዮጵያ ሕገ መንግስት በምርጫ አብላጫውን ድምጽ ያገኘ ፓርቲ መንግስት እንደሚመሰርት የሚያስቀምጥ ሲሆን፤በአዲስ አበባ ምክር ቤት ምርጫ ብልጽግና ፓርቲ ከአብላጫ ድምጽ በላይ አግኝቷል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም