ቀጥታ፡

ኢትዮጵያን ከነታሪኳ ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን

ጎንደር ፤ መስከረም 17/214(ኢዜአ) ''ቀደምት አባቶቻችን ከነ ሙሉ ሰላሟና ክብሯ አስከብረው ያቆዩልንን ኢትዮጵያን ከነታሪኳ ጠብቀን ለትውልድ ማስተላለፍ አለብን'' ሲሉ የምዕራብና የማዕከላዊ ጎንደር ሀገረ ስብከት ሊቀ-ጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል አቡነ ዮሃንስ ተናገሩ፡፡
የመስቀል በዓል በጎንደር ከተማ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በታላቅ ሃይማኖታዊ ስርዓት ተከብሯል፡፡

ሊቀ- ጳጳሱ በበዓሉ ለታደሙ ምእመናን ባስተላላፉት መልዕክት፤ እግዚአብሄር ባይጨመርበትና ባይረዳን ኖሮ ኢትዮጵያ የገጠማትን ክፉ ጊዜና ፈተናዎች ከቶም መሻገር አትችልም ነበር ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በየዘመኑ የገጠማትን ከባድና ውስብስብ ፈተናዎችን ሁሉ በፀሎትና በጽናት አሸንፋ ህዝቦችዋን ከስደት ፣ውርደትና  ባርነት ጠብቃ ዛሬ ላይ ደርሳለች ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ዛሬም እንደትናንቱ ህዝቡ ሰላሙንና አንድነቱን ይበልጥ ሊያጠናክር እንደሚገባ ጠቅሰው፤ ክፉ ጊዜን ለመሻገር መረዳዳት፣ መከባበርና መፈቃቀር አለብን ነው ያሉት፡፡

ስለ ኢትዮጵያ የቆሰሉና የተፈናቀሉ ወገኖቻችን ሁሉ የእኛን እርዳታ እንደሚሹ የተናገሩት ሊቀ-ጳጳሱ፤ የተጎዱትንም በማጽናናት የተፈናቀሉትን ደግሞ በመርዳት ምዕመናን በጋራ መረባረብ አለበት ብለዋል።

''የልማትና የብልጽግና መሰረቱ ሰላም ነው፤ ሰላም ደግሞ ከሩቅ ሳይሆን የሚጀመረው ከአጠገባችን ነው፤በአዲሱ ዓመት ከቤተሰባችን ጀምረን ኢትዮጵያን ሙሉ ሰላሟን ለማጎናጸፍ በህብረት እንነሳ ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡

የመስቀል በዓል ከሃይማኖታዊ እሴቱ ባሻገር ሀገራችንና ህዝባችን ላሉበት ወቅታዊ ሁኔታ ታላቅ መልዕክት አለው ያሉት ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር  ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ ናቸው፡፡

መስቀል ለሌሎች መኖርና ራስን ስለ ፍቅር አሳልፎ  መስጠት በመሆኑ ስለ ሀገርና ህዝባችን ስንል ራስችንን አሳልፈን እንድንሰጥ መስቀሉ ዘወትር ያስታውሰናል ብለዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ ሃይማኖታዊ ስርዓቱ የሚከናወንበትን ስፍራ በዘመናዊ መንገድ ለመገንባት እንዲቻል የተጀመረውን  የዲዛይን ስራ በቅርቡ አጠናቆ ይፋ ለማድረግ መዘጋጀቱንም ከንቲባው አስታውቀዋል።

ሊቀ-ጳጳሱና ከንቲባው በመስቀል አደባባይ የተዘጋጀውን የመስቀል ደመራም በጋራ የለኮሱ ሲሆን በስነ ስርዓቱም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች መታደማቸውን የኢዜአ ሪፖርተር ከጎንደር ዘገቧል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም