"አፍሪካዊያን በጋራ ተሰባስበው ስለትላንት ማንነታቸው የሚያውቁባት ድንቅ አገር ኢትዮጵያ" - ኢዜአ አማርኛ
"አፍሪካዊያን በጋራ ተሰባስበው ስለትላንት ማንነታቸው የሚያውቁባት ድንቅ አገር ኢትዮጵያ"
አዲስ አበባ፣ መስከረም 17/2014 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን በጋራ ተሰባስበው ስለትላንት ማንነታቸው የሚያውቁባት ታሪካዊቷ አገር ኢትዮጵያ ነች" ሲሉ በመስቀል የደመራ በዓል ላይ የታደሙት ናይጄሪያዊያን ጥንዶች ተናገሩ።
የመስቀል ደመራ በአል በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ፕሬዝዳንት ሳህለወረቅ ዘውደ፣ ሌሎች ከፍተኛ የመንግሰት የስራ ሃላፊዎች የአገር ወስጥና የውጭ ቱሪስቶች እንዲሁም በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት ተከብሯል።
የመስቀል በዓል አከባበር በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሳይንስ የትምህርትና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) የማይዳሰስ የዓለም ቅርስ ሆኖ 2005 ዓ.ም ተመዝግቧል።
በበዓሉ ላይ ከተገኙት የውጭ አገራት ቱሪስቶች መካከል ናይጄሪያዊያኑ ጥንዶች ኢትዮጵያን በርካታ አፍሪካዊያን በቅጡ ያልተረዷት የምስጢር ሙዳይ መሆኗን ይናገራሉ።
ናይጀሪያዊዩ ኦኬቺ ኩኮ፣ መሰል ህዝባዊ በዓላት ኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊያንን ማንነት ለማወቅ እንደሚያስችሉ ይናገራሉ።
በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት ሳይንስና ባህል ተቋም (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት የተመዘገበው ይህን ድንቅ ክብረ በዓል የበርካቶች መዳረሻ እንዲሆን ይበልጥ መተዋወቅና መጠበቅ እንዳለበት ገልጸው፤ ይህም ለቱሪዝም ትልቅ ፋይዳ እንዳለው ተናግረዋል።
ይህ በዓል ኢትዮጵያዊያንን የሚያሰባስብ፣ አንድነትን የሚያጠናክር የደስታ በዓላቸው መሆኑን ገልጸዋል።
ኢትዮጵያን አሐዱ ብዬ የረገጥኳት በዚህ ህብረ ቀለም ትዕይንት ባለው በዓል ነው የምትለው ቢኖሳ ኦሱላ በበኩላቸው፤ ምዕመናን እየተመሙ ኃይማኖታዊ በዓላቸውን በደስታ ሲያከብሩ ቀልብ ይስባል ብለዋል።
ኢትዮጵያዊያን ለኃይማኖታቸው ቀናኢና ለአገራቸው ፍቅር ያላቸው ሰዎች ስለመሆናቸው ትዝብታቸውን ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ኢትዮጵያና አፍሪካን ለማስተዋወቅም ትልቅ ሥራ መሥራቱን አስታውሰው፤ ይበልጥ ማስተዋወቅ ቢሰራበት በእንዲህ አይነት በዓላት በርካታ የውጭ ዜጎች እንዲታደሙ ያደርጋል።
ኢትዮጵያ ከተቀረው የአፍሪካ አገራት በተለየ የምዕራቡ ዓለም ባህል ተጽዕኖ ያላሳደረባት፣ ዛሬም የጥንቱን የአፍሪካ ባህል ለዘመናት ጠብቃ ያደረሰች አገር መሆኗን ገልጸዋል።
በዚህም ለአፍሪካዊያን መዲና የሆነችው ኢትዮጵያ አፍሪካዊያን ተሰባስበው ስለትላንት ማንነታቸው የሚመለከቱባትና የሚያውቁቧት የተለየች አገር ነች ብለዋል።
ኢትዮጵያም ይህን ዕድል በመጠቀም አፍሪካዊያንን የማሰባሰብ መስቀልና መሰል በዓላትን በጋራና በደስታ እንዲያከብሩ ማድረግ እንዳለባት ተናግረዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከአሜሪካ ኒዮርክ ከተማ የመጡት ሀሮልድ ኩድ እና ለሁለተኛ ጊዜ መስቀልን ኢትዮጵያ ለማክበር የመጣችው ፖላንዳዊቷ አግኔሽካ በመስቀል ክብረ በዓል ተደንቀዋል።።
በአሜሪካም ሆነ በፖላንድ በርካታ ክብረ በዓላት ቢኖሩም በኢትዮጵያ የተመለከቱትን ያህል ድንቅ አከባበር ግን እንዳልገጠማቸው ይናገራሉ።
ኢትዮጵያን እንዲጎበኙ ለሌሎች ወዳጆቿ ሁሉ መንገር እንደምትሻ አግኔሽካ ትገልጻለች።