በሀዋሳ እና በድሬዳዋ የመስቀል ደመራ በዓል ተከበረ - ኢዜአ አማርኛ
በሀዋሳ እና በድሬዳዋ የመስቀል ደመራ በዓል ተከበረ
ሀዋሳ እና ድሬዳዋ መስከረም 16/2014 (ኢዜአ) የመስቀል ደመራ በዓል በሃዋሳ እና በድሬዳዋ በርካታ የእምነቱ ተከታዮች በተገኙበት በደማቅ ሃይማኖታዊ ስነ-ስርዓት ተከበረ።
በሀዋሳ መስቀል አደባባይ ክብረ በዓሉ ላይ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስትያን ቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ፀሐፊና የሲዳማ፣ የጌዴኦ፣ አማሮና ቡርጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ እንዲሁም የሃዋሳ ከተማ ምክትል ከንቲባ ረዳት ፕሮፌሰር ፀጋዬ ቱኬና ሌሎች የክብር እንግዶች ተገኝተዋል።
በበዓሉ ላይ በሃዋሳ ከተማ አብያተ ክርስትያናት የሚገኙ ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና የሰንበት ትምህርት ቤት ዘማሪያን በዓሉን መሰረት ያደረጉ ሃይማኖታዊ ዝማሬዎችና ትርኢቶችን አቅርበዋል።
የእምነቱ ተከታይ የሃዋሳ ከተማ ነዋሪዎችም በባህላዊና ሃሀይማኖታዊ አለባበስ አሸብርቀው በክብረ በዓሉ ላይ የታደሙ ሲሆን ካህናትና የበሰንበት ትምህርት ቤት ወጣቶችም ለበዓሉ ያሬዳዊ ህብረ ዝማሬ አቅርበዋል።
በተመሳሳይ የመስቀል ደመራ በዓል በድሬዳዋ ምድር ባቡር በደማቅ ሃይማኖታዊ ስነስርዓት ተከብሯል።
በዓሉ ማምሻውን የተከበረው የሃይማኖት አባቶች፣ ካህናት፣ ዘማሪያንና ቁጥራቸው በብዙ ሺህ የሚገመቱ የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሃይማኖት ተከታዮች በተገኙበት ነው።
በበዓሉ ላይ የተገኙት የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አህመድ መሐመድ ቡኽ ለክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ መልክታቸውን ገልጸዋል
አገርን ለማዳንና አስተማማኝ ሰላም ለማስፈን ኢትዮጵያዊያን እያደረጉት ያለው ሁለንተናዊ ድጋፍ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ተናግረዋል።
"በአሉን ስለ አገር ሉአላዊነት፣ ሰላም እና አንድነት በማሰብ ማክበር ይገባናል" ሲሉም አክለዋል።
በተለይም የተቸገሩና በግንባር አገርን ለማዳን የዘመቱ ወንድሞችን ቤተሰቦች በመደገፍና የእርሻ ማሳቸውን በመንከባከብ ማገዝ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
ኢትዮጵያዊያን የሀገርን ሉአላዊነትና ሰላም እንዲጠበቅ ሽብርተኛውን ህወሓት ለመደምሰስ እያደረጉ ያሉትን ርብርብ አጠናክረው እንዲቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል።