ቀጥታ፡

በአማራ ክልል ለሚገኙ የጤና ተቋማት የ217 ሚሊዮን ብር የቁሳቁስ ድጋፍ ተደርጓል---የጤና ሚኒስቴር

መስከረም  16/2014 (ኢዜአ) በአማራ ክልል የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ በሥራ ጫና ውስጥ ላሉ የጤና ተቋማት የ217 ሚሊዮን ብር የመድሃኒትና ሌሎች ቁሳቁስ ድጋፍ መደረጉን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።

በጤና ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ የሚመራ ቡድን በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን አካባቢዎች ከጎበኘ በኋላ ከአማራ ክልል ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር ዛሬ ተወያይቷል።

በውይይቱም አሸባሪው ህወሓት በወረራቸው አካባቢዎች የጤና ተቋማት በመዘረፋቸውና በመውደማቸው ከ6 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ህዝብ ከጤና አገልግሎት ውጭ መሆኑን ተገልጿል።

ሚኒስትሯ ዶክተር ሊያ ታደሰ ከውይይቱ በኋላ ለጋዜጠኞች እንዳሉት የአማራ ክልል የህልውና ዘመቻውን ተከትሎ ከፍተኛ ጫና ውስጥ ይገኛል።

ጦርነቱ በክልሉ የሚያስከትለውን ችግር ከግምት ውስጥ በማስገባት ሚኒስቴሩ ከሰኔ ወር ጀምሮ በመድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ በኩል የ217 ሚሊዮን ብር የመድሀኒትና የቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን ተናግረዋል።

እንደእሳቸው ገለጻ በተደረገው ድጋፍ በንፋስ መውጫና መቄት ወረዳዎች በጦርነቱ ጉዳት የደረሰባቸውን የጤና ተቋማት ወደ ስራ ለማስገባት የሚያስችል ግብአት የማሟላት ስራ ተሰርቷል።

"ሚኒስቴሩ ከክልሉ ጋር በመተባበር ለድንገተኛ ህክምና አገልግሎትና ተፈናቅለው በመጠለያ የሚገኙ ወገኖች በተንቀሳቃሽ የሕክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ሁኔታ እያመቻቸም" ይገኛል ብለዋል።

"ጦርነት በተካሄደባቸው የክልሉ አካባቢዎች የሚገኙ ጤና ተቋማት ላይ ከፍተኛ ዝርፊያና ውድመት ደርሷል" ያሉት ሚኒስትሯ፣ በቀጣይም ከረጂ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ተቋማቱን ወደ አገልግሎት ለመመለስ እንደሚሰራ አመልክተዋል።

የአማራ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ፋንታ ማንደፍሮ በበኩላቸው የህልውና ዘመቻው ከተጀመረ አንስቶ ሚኒስቴሩ የመድሃኒት፣ የህክምና መሳሪያና ሌሎች ቁሶችን እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።

ዶክተር ማንደፍሮ እንዳሉት ነጻ በወጡ አካባቢዎች በጤና ተቋማቱ ላይ የደረሰው ውድመት ከፍተኛ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በሚንስቴሩና በክልሉ ብቻ ተቋማቱን ቀድሞ ወደ ነበሩበት ደረጃ ለመመለስ ያስቸግራል።

በመሆኑም ሚንስቴሩ ከዓለም አቀፍ ግብረ ሰናይ ድርጅቶችና ከሌሎች ክልሎች ጋር በመተባበር የጀመረውን ድጋፍ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

"በሸባሪው ህወሓት ወረራ 25 ሆስፒታሎች፣ 277 ጤና ጣቢያዎች፣ 1ሺህ 129 የጤና ኬላዎችና ሁለት የደም ባንኮች ከአገልግሎት ውጭ ሆነዋል" ያሉት ደግሞ የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ታሪኩ በላቸው ናቸው።

እንደ ሀላፊው ገለጻ በጤና ተቋማቱ ላይ በደረሰው ዘረፋና ውድመት ከ6 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ህዝብ መሰረታዊ የጤና አገልግሎት ማግኘት አልቻለም።

የወደሙ የጤና ተቋማትን ቀድመው ወደ ነበሩበት ደረጃ ለመመለስ ጊዜ ስለሚወስድ ከጤና ሚንስቴርና ሌሎች ረጅ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ድንገተኛ ህክምና የሚሰጠበት ሁኔታ እየተመቻቻ መሆኑን ተናግረዋል።

"በህወሓት ወረራ ከተፈጸመባቸው ከካባቢዎች በርካታ ንጹሃን ዜጎች ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ" ያሉት አቶ ታሪኩ፣ እነዚሀን በተንቀሳቃሽ የህክምና አገልግሎት ተደራሽ ለማድረግ ጥረት መደረጉን ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም