ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ የያዘችው እውነት እንደ ደመራው ብርሃን ደምቆ ይበራል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) "ኢትዮጵያ የያዘችው እውነት እንደ ደመራው ብርሃን ደምቆ ይበራል" ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ በመስቀል አደባባይ በተከበረው የመስቀል ደመራ በአል ላይ በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።

ምክትል ከንቲባዋ በመልእክታቸው ክፉዎች መስቀሉን በቆሻሻ ክምር ሊደብቁት ሞክረው እንዳልተሳካላቸው አንስተዋል።

የመስቀሉን እውነት በቆሻሻ ሊደብቁት እንደሚከሩት ሁሉ አሁን ላይ ኢትዮጵያ የያዘችውን እውነት ለመደበቅና ለማድበስበስ የሚጥሩ የውጭና የውስጥ ሃይሎች እንዳሉ ገልጸዋል።

የተፈጥሮ ሃብታችንን በእነርሱ ፈቃድ እንድንጠቀም የሚሹ ሃይሎች ልማታችንን ለማደናቀፍ እየጣሩ ሲሆን እኛ ካላስተዳደርናት ኢትዮጵያ ትፍረስ ብለው ቆርጠው የተነሱ ከሃዲዎች መኖራቸውንም ጠቅሰዋል።

ሆኖም ኢትዮጵያ በፈጣሪዋና ህዝቦቿ አሸናፊ ትሆናለች፤ የያዘችው እውነታም እንደ ደመራው ብርሃን ደምቆ ይበራል ብለዋል ምክትል ከንቲባዋ።

በነጩ ቤተ መንግስት በመገኘት የኢትዮጵያን እውነታ ለማስረዳት ለጣሩ የሃይማኖት አባቶች እንዲሁም የኢትዮጵያን ክብርና ሉአላዊነት ለማስከበር በመላው ዓለም ጥረት እያደረጉ ላሉ ሁሉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

መላው የኢትዮጵያ ህዝቦች አሸባሪውን የህወሃት ቡድን በጋራ እንታገለው በማለትም ጥሪያቸውን በማቅረብ የብልፅግና ጉዟችንን ጀምረናል የሚያስቆመን ሃይል አይኖርም ብለዋል።

በመላው ዓለም የምትገኙ ኢትዮጵያዊያን የአገራችንን ክብር የማስጠበቅ በሁሉም አጋጣሚ ድምጽ ለመሆን የያዛችሁት ጥረት በእጅጉ የሚደነቅ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዶክተር ሂሩት ካሳው፤ በየተሰማራንበት በትጋት በመስራትና እኩይ ተግባራትን በመመከት ለአገራችን እድገት ልንሰራ ይገባል ብለዋል፡፡

የቀደምት አባቶቻችን ያወረሱንን ባህላዊ እሴቶች ከነሙሉ ክብራቸው ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ አለበን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

መስቀል ከሃይማኖታዊ እሴቱ በተጨማሪ አገራዊ እሴት በመሆኑ ሁሉም ሊጠብቀውና ሊንከባከበው ይገባል ብለዋል።

ኢትዮጵያዊያን ፍቅርና አብሮነትን እንስበክ፣ እንረዳዳ፣ እንተጋገዝ፣ በጋራ ሆነን የአገራችንን ሰላም እና ልማት እናስቀጥል ሲሉም መልእክታቸውን አስተላልፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም