መስቀል የእርቅና ሰላም ተምሳሌት በመሆኑ በየጊዜው እርቅና ሰላማችንን እውን ማድረግ አለብን - ኢዜአ አማርኛ
መስቀል የእርቅና ሰላም ተምሳሌት በመሆኑ በየጊዜው እርቅና ሰላማችንን እውን ማድረግ አለብን
መስከረም 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) "መስቀል የእርቅና ሰላም ተምሳሌት በመሆኑ በየጊዜው እርቅና ሰላማችንን እውን ማድረግ አለብን" ሲሉ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያሪክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ጥሪ አቀረቡ፡፡
ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ በተከበረው የመስቀል ደመራ በአል ላይ በመገኘት መልእክት አስተላልፈዋል።
በመልእክታቸውም መስቀል በፈጣሪ እና በሰው ልጆች መካከል እርቅ የወረደበት፤ ሰውም ከፍዳ መርገምት የዳነበት መሆኑን ገልጸዋል።
በመሆኑም መስቀል የእርቅና ሰላም ተምሳሌት ስለሆነ ሁላችንም ለእርቅና ሰላም እውን መሆን መትጋት አለብን ብለዋል።
የሰው ልጆች እርስ በእርስ እርቅ ማድረግና ለሰላም መትጋት አለባቸው ያሉት ብፁእነታቸው ዓለም ሰላም የምታገኘው በሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ስነ ፍጥረትም ሰላም ሲሆኑ ነው ያሉት።
በመሆኑም ሁሉም ለሰላምና አንድነትና በጋር ጠንክሮ መስራት አለበት ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
በክብረ በዓሉ ላይ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ፣ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትሯ ዶክተር ሂሩት ካሳው፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንዲሁም በርካታ የእምነቱ አባቶችና እንግዶች ተገኝተዋል።