በተመረጡ 69 ከተሞች ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በተመረጡ 69 ከተሞች ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት እየተሰራ ነው
ባህርዳር፣ መስከረም 16/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በተመረጡ 69 ከተሞች ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት አቅዶ እየሰራ መሆኑን የትራንስፖርት ሚኒስቴር አስታወቀ።
"ባህር ዳርን ወደ ቀደመ የብስክሌት ከተማነት እየመለስን፣ የተፈናቀሉ ወገኖቻችንን እንርዳ" በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በከተማዋ የብስክሌት ቀን ተከብሮ ውሏል።
በሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ የመንገድ ትራንስፖርት አገልግሎት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ፈቲሃ ደድገባ እንደገለጹት፣ ሞተር አልባ ትራንስፖርትን በከተሞች ማስፋፋት የዘላቂ ልማት ግብ ሆኖ እየተሰራ ይገኛል።
የብስክሌት ትራንስፖርት አገልግሎት ሁሉም ማህበረሰብ ሊጠቀመው የሚገባና ከአየር ብክለት ነፃ የሆነ፣ ጤናማና ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያም በቀጣዮቹ 10 ዓመታት በተመረጡ 69 ከተሞች ሞተር አልባ የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስፋፋት ዕቅድ ተይዞ እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
"ባህር ዳርን ወደቀደመ የብስክሌት ከተማነት ለመመለስ ዛሬ የተጀመረው እንቅስቃሴም ከተማዋ የቱሪስት መስህብነቷን ይበልጥ ለማሳደግና የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የጎላ ድርሻ አለው" ብለዋል።
በፌዴራልም ሆነ በክልሎች አዲስ የሚሰሩ መንገዶች የሞተር አልባ ትራንስፖርትን ግምት ውስጥ አስገብተው እንዲገነቡና ነባር መንገዶችም የብስክሌትና የእግረኛ መንገድ እንዲኖራቸው ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ኃላፊዋ ገልጸዋል።
"የብስክሌት ትራንስፖርት እንዲስፋፋና ማህበረሰቡ የእግር ጉዞን ባህሉ እንዲያደርግ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከክልሎች ጋር ተቀናጅቶ ይሰራል" ብለዋል።
"ባህር ዳር ከተማ ቀደም ሲል ወደነበረችበት የብስክሌት ታሪክ እንድትመለስ የሚገነቡ መንገዶች ብስክሌትን ታሳቢ እንዲያደርጉ ጥረት እናደርጋለን" ያሉት ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ አቶ ባየ አለባቸው ናቸው።
ለዚህም በከተማዋ ከፖሊ እስከ ፔዳ ያለው መስመር ለብስክሌት ትራንስፖርት እንዲያገለግል ቅድመ ሁኔታዎችን የማመቻቸት ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
"በቀጣይ በፌደራልም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ የሚገነቡ አዳዲስ መንገዶች ለብስክሌት ጉዞ የሚያገለግሉ ሆነው እንዲገነቡ አስፈላጊው ጥረት ይደረጋል" ሲሉም አረጋግጠዋል።
አቶ ባየ እንዳሉት የብስክሌት ትራንስፖርት በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርጽ የከተማ አስተዳደሩ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል።
ህብረተሰቡ የብስክሌት ቀንን ከማክበር ጎን ለጎን በአሸባሪው ህወሓት ለተፈናቀሉ ወገኖች የሚጠበቅበትን ድጋፍ በማድረግ የድርሻውን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል።
የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶክተር ፍሬው ተገኝ በበኩላቸው የአደጉ ሀገራት የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ ብስክሌትን መጠቀም የዘወትር ተግባራቸው መሆኑን ተናግረዋል።
"ዩኒቨርሲቲው የባህር ዳር ከተማን መዋቅራዊ ፕላን አዘጋጅቶ ለከተማ አስተዳደሩ በማስረከብ የብስክሌት ትራንስፖርት እንዲስፋፋ የበኩሉን እያደረገ ይገኛል" ብለዋል።
በቀጣይም ከተማዋ የቀደመ የብስክሌት ትራንስፖርት ባህሏ እንዲመለስ ከሚሰሩ የህብረተሰብ ክፍሎችና ከከተማ አስተዳደሩ ጋር እንደሚሰራም አረጋግጠዋል።
"በከተማዋ የብስክሌት ባህል እንዲመለስ ዛሬ የተጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል" ያሉት ደግሞ የከተማዋ ነዋሪ አቶ መልካሙ አበበ ናቸው።
ለረጅም ዓመታት ብስክሌት ማሽከርከራቸውን አስታውሰው፤ ከከተማዋ ዕድገት ጋር ተያይዞ በተፈጠረ የትራፊክ መጨናነቅ ለማቆም መገደዳቸውን ተናግረዋል።
ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲና ከተማ አስተዳደሩ በትበብር ባዘጋጁት ፕሮግራም ከቀድሞው ጊዮን ሆቴል እስከ ባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ዊዝደም ህንፃ ድረስ የብስክሌት ግልቢያ ተከናውኗል።
ዩኒቨርሲቲው በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ ከፖሊ እስከ ፔዳ በራሱ ወጪ ለሚያስገነባው የብስክሌት መንገድም ዛሬ የመሰረት ድንጋይ ተቀምጧል ።