የክልሎች ልዩ ሃይሎች ለመተከል ዞን ሰላም ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሎች ልዩ ሃይሎች ለመተከል ዞን ሰላም ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በቅንጅት እየሰሩ ነው
አሶሳ፣ መስከረም 16/ 2014 (ኢዜአ) በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የመተከል ዞንን ሠላም ወደ ነበረበት ለመመለስ የክልሎች ልዩ ሃይሎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ተቀናጅተው እየሰሩ መሆኑን የክልሉ ሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ አስታወቀ።
የመተከል ዞን በአራቱም ማዕዘን መላ ኢትዮጵያዊያን ከፍጻሜ እንዲደርስ ርብርብ እያደረጉበት ያለው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት መገኛ ነው፡፡
አሸባሪው ህወሓት ይህን የኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበት ፕሮጀክት ለማደናቀፍና የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ መተከልን የጦርነት አውድማ ለማድረግ ተግቶ መስራት ከጀመረ ሰነባብቷል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሃሚድ እንደሚሉት የህወሓት የጥፋት ቡድን ይህን እኩይ ዓላማውን ለማሳካት ከውስጥ እና ከውጪ የኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር ተቀናጅቶ እየሠራ ነው።
በመሆኑም ይህን የጥፋት ድርጊት በመመከት የመተከልን ሠላም ለመመለስ የፌዴራልና የክልል መንግስታት ለችግሩ ትኩረት ሰጥተው በቅንጅት እየሰሩ መሆኑን ለኢዜአ ተናግረዋል።
አቶ ሙሳ እንዳሉት የመተከልና አካባቢውን ሰላም ለመመለስ በተለይ የሀገር መከላከያ ሠራዊት የከፈለውና እየከፈለው ያለው መስዋዕትነት ከፍተኛ ነው።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ የአማራ፣ የሲዳማ፣ የጋምቤላ፣ የደቡብ እና የሌሎችም ክልሎች ልዩ ሃይሎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር ተቀናጅተው የዞኑን ሠላም ለመመለስ የተጠናከረ የጸጥታ ማስከበር ሥራ እየሰሩ መሆኑን አስረድተዋል።
ለዚህም በቅርቡ ድንበር አቋርጠው ሲገቡ በጸጥታ አስከባሪ ሃይሎቹ የተደመሰሱ ከ170 የሚበልጡ የጥፋት ቡድኑ ተላላኪዎችን አቶ ሙሳ በአብነት ጠቅሰዋል።
በአካባቢው ሰላምን በማስከበር እየተገኘ ያለውን ውጤት ለማደናቀፍ የህወሓት ርዝራዦች የዞኑን ህዝብ በሀሰተኛ ወሬ ለማደናገር እየሞከሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
“የመተከል ዞን የኢትዮጵያዊያን ፕሮጀክት የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገኛ በመሆኑ የክልሉ መንግስት የአካባቢውን ሰላም ለማስከበር ኮማንድ ፖስትን ጨምሮ ከየትኛውም ህጋዊ የጸጥታ አስከባሪ ሃይል ጋር ተቀናጅቶ መስራቱን ይቀጥላል” ሲሉም አቶ ሙሳ አክለዋል።
ከአሶሳ ከተማ ነዋሪዎች መካከል አቶ ኦላና ደግፌ በአሁኑ ወቅት ልዩ ሀይሎቹ በጋራ መስራታቸው እርስ በእርስ የመደጋገፍ ባህልን ከማጠናከር ባለፈ በአካባቢው ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን ጠቀሜታው የጎላ መሆኑንም ገልጸው “ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያዊ አንድነት እየተጠናከረ እንዲመጣ ያግዛል” ብለዋል።
ህወሓት በመተከል ዞን የጸጥታ ችግር እንዲፈጠር የሚያደርግበት ዋና ዓላማ የሕዳሴ ግድቡን ግንባታ ለማደናቀፍ መሆኑንና ይህም እንዳልተሳካለት የተናገሩት ደግሞ አቶ ጌትነት ብርሃኔ የተባሉ ሌላው የአሶሳ ከተማ ነዋሪ ናቸው።
ልዩ ሃይሎቹ ከሃገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት በመተከል የጀመሩትን ሰላምን የማስፈን ሥራ በመደገፍ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።
በአካባቢው ዘላቂ ሠላም እንዲሰፍን አዲስ የሚቋቋመው የፌደራል መንግስት ዋነኛ የትኩረት አቅጣጫው አድርጎ እንዲሰራም አቶ ጌትነት ጠይቀዋል።