ቀጥታ፡

የአውሮፓ ሕብረት አሸባሪው ህወሓት የሚያሰራጨውን ሐሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ በመገንዘብ ለኢትዮጵያ አጋርነቱን ሊያሳይ ይገባል

መስከረም 16 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአውሮፓ ሕብረት አሸባሪው ህወሓት የሚያሰራጨውን ሐሰተኛ መረጃና የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ በመገንዘብ ለኢትዮጵያ አጋርነቱን በማሳየት ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጎን እንዲቆም ተጠየቀ።

የፊልም ባለሙያው አርቲስት ቴዎድሮስ ተሾመ በአውሮፓ ህብረት የአለም አቀፍ ድጋፍ ለኢትዮጵያ አስተባባሪ ኤዛቤል ሁበርት እና ማርክ ስታልማንስ በህብረቱ የምስራቅ አፍሪካ፣ የአፍሪካ ቀንድና የማዕከላዊ አፍሪካ ጉዳዮች ቡድን መሪ በወቅታዊ የኢትዮጵያ ጉዳዮች ዙሪያ ማብራሪ ሰጥቷል።

አርቲስት ቴዎድሮስ በማብራሪያው የአፍሪካ አገራት በድህነት እንዲቆዩ የተገደዱት በከፍተኛ የእርዳታ ጠባቂነት ስሜት መያዛቸው፣ የቀኝ ግዛት አካሄዶችና በመሪዎች ከህዝብ ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም መቆምና የጭቆና አገዛዝ የተነሳ ነው ብሏል።

“አሁን ግን በሌሎች የመረዳትና የመደገፍ ጊዜው ያበቃ ይመስላል” በማለት አፍሪካውያን በራሳቸው እንቁ ልጆች የመመራትና የተፈጥሮ ሃብታቸውን ወደ ተግባር በመጠቀም ከድህነት ለመውጣት መነሳታቸውን ገልጿል።

“በቀኝ ገዢዎች የተሰራባቸውን የጠባቂነት ስሜት በመጣል በአፍሪካ በቢሊዮን የሚቆጠሩ አእምሮዎች ቀጣይነት ያለውን ብልጽግና ለማሳካት መነሳሳታቸውን በመግለጽ ኢትዮጵያም የዚህ መሪ መሆኗን ከታሪክ መማር እንችላለን በማለት ነው” ያብራራው።

ታሪክ እንደሚመሰክረው ኢትዮጵያ ከአለም ቀደምት አገራት በመሆን በኢኮኖሚ በፖለቲካ እና በሌሎች መስኮች መሪ በመሆን ነጻነቷን አስጠብቃ ቆይታለች ያለው አርቲስት ቴዎድሮስ፤ “ኢትዮጵያውያን አንድ በመሆንም አገራቸውን ከጠላት በመጠበቅ አጽንተዋል” ብሏል።

ከዘመነ መሳፍንት በኋላ የተነሱ የኢትዮጵያ መሪዎችና ኢትዮጵያውያን ገድል ይመሰክራል የአድዋ ድልም የዚህ ማሳያ ነው በማለት አስረድቷል።

“ከደርግ መንግስት መውደቅ በኋላ ወደ ስልጣን የመጣው የአሸባሪው ህወሓት ቡድን ለዘመናት የቆየውን የኢትዮጵያን የውስጥ ግዛት በራሱ መንገድ በመከፋፈልና ኢትዮጵያውያንን በጎጥና በዘር እንዲለያዩ ርዕዮት አለም በመፍጠር ህዝቡ አንድ እንዳይሆን አድርጎ ቆይቷል” ነው ያለው አርቲስት ቴዎድሮስ።

አሸባሪው ቡድን ይዞት የመጣውን የመገንጠል ስትራቴጂ ለማሳካትም የትግራይን ክልል ከሱዳን ድንበር ጋር ለማገናኘት መስራቱን አስታውሷል።

“ቡድኑ በነበረው 27 አመታት የግዛት ዘመን የሽብር ቡድኑ አጋር አካለት ብቻ በሁሉም መስክ እንዲሰሩ በማድረግ የአገሪቷ ሃብት እንዲመዘበር እና ከ35 ቢሊዮን ዶላር በላይ የህዝብ ሃብት ከአገር እንዲሸሽ አድርጓል” በማለት ማብራሪያ ሰጥቷል።

የሽብር ቡድኑ ከዚህ በማለፍ በጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ለ20 አመታት የአገሪቱን ዳር ድንበርና የትግራይን ህዝብ ሲጠብቅ የነበረውን የመከላከያ ሰራዊት በማጥቃት በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮችን በመግደል አገር የማፍረስ ተግባር ውስጥ መግባቱን አመልክቷል።

መንግስት ይሄን ተከትሎ ወደ ሕግ ማስከበር ዘመቻ በመግባት አሸባሪው ቡድንን እንቅስቃሴ ቢገታም የሽብር ቡድኑ አባላት ባሰራጩት ሀሰተኛ መረጃና ፕሮፖጋንዳ አለም አቀፉ ማህበረሰብ የተሳሰተ አቋም እንዲዝ አድርጓል።

በአሁኑ ወቅትም የኢትዮጵያ መንግስት አገርን ለማፍረስ የተሰማራን ቡድን ለህግ ተጠያቂ ለማድረግና አገርን ከመፍረስ ለማዳን እየሰራ እንደሚገኝ ገልጿል።

የአውሮፓ ሕብረትም ከዚህ በመነሳት ቡድኑ የሚያሰራጨውን ሐሰተኛ መረጃና የተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ በመገንዘብ ለኢትዮጵያ አጋርነቱን በማሳየት ከኢትዮጵያና ከኢትዮጵያውያን ጎን እንዲቆም ጠይቋል።

በማብራሪያው የተሳተፉት የህብረቱ አባላት በበኩላቸው በማብራሪያው በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊና ፖለቲካዊ ሁኔታ በበቂ ሁኔታ መረዳታቸውን ገልጸዋል።

አክለውም የአውሮፓ ህብረት የጠነከረች ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በመሆንም በተለያዩ ድጋፎች ዙሪያ በጋራ እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም