ቀጥታ፡

የማኅበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ላይ የሚሰሯቸውን ዘገባዎች አጠናክረው ይቀጥላሉ

መስከረም 15/2014(ኢዜአ) ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ የያዘችውን የፍትሃዊ ተጠቃሚነት መርህ በሚሰሯቸው ዘገባዎች ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ማሳወቃቸውን አጠናክረው እንደሚቀጥሉ የማኅበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች ገለጹ።

የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ሕዝባዊ ተሳትፎ አስተባባሪ ብሔራዊ ምክር ቤት ጽህፈት ቤት  ከማኅበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች ጋር ተወያይቷል።

ውይይቱ ግድቡን በተመለከተ ሁሉም በየሙያ መስኩ የሚሳተፍበትና መረጃ  የሚለዋወጥበት "ጥምረት ለፍትህ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ ትስስር" ላይ ያተኮረ ነው።

ትስስሩ ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ ላይ ያላትን እውነት ለዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ለማሳወቅ በተበታተነ መልኩ ሲከናወን የነበረውን ተግባር በተቀናጀ መልኩ ማድረስ የሚያስችል ነው።  

የውይይት መድረኩ የማኅበራዊ ሚዲያ ባለሙያዎች በግድቡ ዙሪያ የጀመሯቸውን ተግባራት በትስስሩ አጠናክረው መሄድ በሚችሉበት አግባብ ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል።   

የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎቹ ግድቡን በተመለከተ ስላከናወኗቸው ተግባራት ገልጸዋል።

ባለሙያዎቹ መገናኛ ብዙኃን በግድቡ ዙሪያ እየሰሩት ያለው ሥራ እየተጠናከረ መምጣቱን ገልጸው፤ በቀጣይም መጠናከር እንደሚገባቸው ተናግረዋል።

ሁሉም ዜጋ ኢትዮጵያ ያላትን እውነት ለዓለምአቀፉ ማህበረሰብ በማስገንዘብ ረገድ ኃላፊነቱን መወጣት እንዳለበትም ገልጸዋል።

የጽህፈት ቤቱ የሕዝብ ግንኙነትና ሚዲያ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ኃይሉ አብርሃም እንዳሉት፤ ለግድቡ ሀብት ለማሰባሰብና ፍትሃዊ የጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ተመስርቶ እየተገነባ ያለ መሆኑን ለማስገንዘብ በተናጠል ሲሰራ ነበር።

የተከናወኑ ተግባራት ለውጦች እንዲመጡ ያደረጉ መሆናቸውን ገልጸው፤ በዘመናዊ የመረጃ ቴክኖሎጂ ከመደገፍ አንጻር ግን አሁንም የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ አስረድተዋል።

በአገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆች የግድቡን ሥራዎች በተጠናከረና በዘመናዊ መልኩ በመደገፍ ለማከናወን የትስስር ድረ-ገጾችና የማህበራዊ ሚዲያ ገጾች መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።

እነዚህን ሥራዎች የማስተዋወቁ ተግባር እየተከናወነ መሆኑንና ቀጣይነትም ያለው እንደሆነ ተናግረዋል።   

መገናኛ ብዙኃን የሚሰሯቸውን ሥራዎች የጋራ በማድረግ፣ አስተሳስረውና አቀናጅተው መቀጠል እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።  

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም