የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለመከላከያ ሠራዊት ከ233 ሚሊዮን ብር በላይ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ አደረገ

67

መስከረም 15/2014 (ኢዜአ) የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለአገር ህልውና ዘመቻ ለተሰለፈው መከላከያ ሠራዊት በሦስት ዙር ከ233 ሚሊዮን ብር በላይ የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ።

ዛሬ ግምታቸው 24 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚደርስ 416 ሰንጋዎችን አበርክቷል።

ክፍለ ከተማው ከህብረተሰቡ፣ ከባለሀብቶች እንዲሁም ከተለያዩ ድርጅቶች ያሰባሰበውን ድጋፍ  ለመከላከያ ሠራዊቱ አስረክቧል።

ክፍለ ከተማው የዛሬውን ጨምሮ በሦስት ዙር ከ233 ሚሊዮን ብር በላይ የዓይነት እና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተመላክቷል።

የኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሙቀቱ ታረቀኝ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ መከላከያ ሠራዊትን መደገፍ አገርን ማሳደግ ነው።

ክፍለ ከተማው በሦስት ዙር ድጋፍ ሲያሰባስብ መቆየቱን አስታውሰው፤ በዛሬው ዕለትም ግምታቸው 24 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚሆን 416 ሰንጋዎች በድጋፍ ማበርከቱን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለመቅበር ሠራዊቱ እያደረገ ላለው ተጋድሎ ድጋፉ መሰባሰቡንም ጠቁመዋል።

ለህልውና ዘመቻው ጥሪም ከክፍለ ከተማው በመጀመሪያ ዙር 474 ወጣቶች በሁለተኛው ዙር 340 ወጣቶች አገራዊ ጥሪውን በመቀበል ወደ ሥልጠና መግባታቸውን ተናግረዋል።

ድጋፉን የተረከቡት በመከላከያ ሚኒስቴር የህብረት ሎጂስቲክ ዋና መምሪያ የፋይናንስ ሥራ አመራር ዳይሬክተር ብርጋዴር ጄነራል አስረስ አያሌው ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ክፍለ ከተማው አገራዊ ጥሪ ከተጀመረበት ወቅት ጀምሮ እያደረገ ባለው ድጋፍ ኢትዮጵያን የማዳን ሥራውን በተግባር መስመስከሩን ገልጸዋል።

አሸባሪው ህወሓት ግብአተ መሬት በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚፈጸም እና ህዝቡ ወደነበረበት ሰላም እንደሚመለስ ጠቁመዋል።

አሸባሪው ህወሓትን ከሥር መሰረቱ ለመንቀል ዜጎች የጀመሩትን ድጋፍ  አጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ብርጋዴር ጄነራል አስረስ  አክለዋል።

የክልሎች ብሔራዊ ድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዶክተር ተመስገን ቡርቃ በበኩላቸው፤ "ከተማ አስተዳደሩ ሁለት ነጥብ አንድ ቢሊዮን ብር ድጋፍ ለመሰብሰብ አቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነው" ብለዋል።

እስካሁን ከተማው ካበረከታቸው ሰንጋዎች ውስጥ ከአንድ ሺህ በላይ የሚሆኑት ከኮልፌ ቀራንዮ ክፍለ ከተማ የተገኙ መሆናቸውን ነው የገለጹት።

ይህም ከተደረገው ድጋፍ 53 በመቶውን የሚይዝ መሆኑን ነው ዶክተር ተመስገን የጠቆሙት።

ክፍለ ከተማው ይህንን ሀብት በማሰባሰብ ረገድ ላከናወነው ተግባር ምስጋናቸውንም አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም