የሚመሰረተው መንግስት ለሠላምና ደህንነት እና ለውስጥ ጉዳዮች ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት አለበት

96

መስከረም 15/2014 (ኢዜአ) በመጪው ሣምንት የሚመሰረተው አዲስ መንግስት በሠላምና ደህንነት እና በውስጥ ጉዳዮች ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት አለበት ሲሉ ምሁራን ተናገሩ።

በ6ኛው አገራዊ ምርጫ በአብላጫ ድምጽ ያሸነፈው የብልፅግና ፓርቲ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም መንግሥት ይመሰርታል።

ኢዜአ ከአዲሱ መንግስት ምን ይጠበቃል? ሲል ያነጋገራቸው ምሁራን በሠላማዊ የምርጫ ሂደት አልፎ መንግስት መመስረት ለቀጣዩ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉልህ አስተዋፅኦ እንዳለው ገልጸዋል።

የስትራቴጂያዊ ጉዳዮች ኢንስቲትዩት የውቅረ መንግስትና አገር ግንባታ ተመራማሪ በኢትዮጵያ የሚስተዋሉት ችግሮች ስር የሰደዱ በመሆናቸው በአንድ ጊዜ አይፈቱም ይላሉ።

በመሆኑም ችግሮቹን ለይቶ አንገብጋቢ የሆኑትን በአጭር ጊዜ መፍታት ይገባል ነው ያሉት።

በተለይም በአገሪቷ እየተስተዋሉ ያሉ የሠላምና ደህንነት ችግሮችን ጊዜ ሳይሰጥ በአጭር ጊዜ መፍታት አለበት ያሉት አቶ ወንድወሰን ንጉሴ ናቸው።

አዲስ የሚመሰረተው መንግስትም ሠላምና ደህንነት፣ የተቋማት ግንባታ እና የኑሮ ውድነት ላይ ቅድሚያ ሰጥቶ ሊሰራ ይገባል ሲሉ ሃሳብ ሰንዝረዋል።

አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የሕዝቡን ፍላጎት ለማሟላት ቅድሚያ ሰጥቶ መስራት እንዳለበት የተናገሩት ዶክተር ተስፋዬ ፤በዛብህ ደግሞ አዲስ የሚሾሙ አመራሮች እውቀትና ክህሎት፣ የአገር ፍቅር ኖሯቸው ለሕዝብ የወገኑ መሆን እንደሚገባቸው አንስተዋል።

የዶክተር ተሰፋዬን ሃሳብ የሚጋሩት ዶክተር መሀመድ ሰይድም ሠላምና ደህንነት ማረጋገጥ በዋነኝነት የመንግስት ተግባር ቢሆንም ማኅበረሰቡም ሠላሙን ማምጣት ይጠበቅበታል ብለዋል።

በኢትዮጵያ ላይ የሚደርሰውን የውጭ ጫና ለመቋቋም የውስጥ ችግሮችን መፍታት ላይ ትኩረት አድርጎ መስራት ከአዲሱ መንግስት ይጠበቃል ያሉት ደግሞ አቶ ጋሻው አይፈራም ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም