ቀጥታ፡

አንድነታችንን አጠናክረን አዲስ የሚመሰረተውን መንግስት ማገዝ ይጠበቅብናል

መስከረም 15/2014(ኢዜአ) "የጀመርነውን አንድነት አጠናክረን አዲስ የሚመሰረተውን መንግስት ማገዝ ይጠበቅብናል" ሲል አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ተናገረ።

የሚመሰረተው አዲስ መንግስት ሕዝብ የመምራት ብቃት ያላቸው አመራሮችን ወደ ኃላፊነት ማምጣት እንዳለበትም ገልጿል።

ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም በተካሄደው አገራዊ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት ኢትዮጵያዊያን የሌሊት ቁርና ዝናብ ሳይበግራቸው በነቂስ በመውጣት ድምጻቸውን ለመረጡት ፓርቲ ሰጥተዋል።

ምርጫው በአገሪቷ ከተካሄዱ ምርጫዎች በተሻለ ሠላማዊ፣ አሳታፊና ዴሞክራሲያዊ የነበረ ሲሆን፤ ይህም ኢትዮጵያዊያን የአገራቸውን ፖለቲካ ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር ያላቸውን ቁርጠኝነት ያመላከተ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ይፋ ባደረገው ውጤትም የብልጽግና ፓርቲ መንግስት መመስረት የሚያስችለውን አብላጫ ድምጽ ማግኘቱ ይታወቃል።

በዚሁ መሰረት አዲሱ መንግስት መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም ይመሰረታል።

አትሌት ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ ለኢዜአ እንደተናገረው፤ የሚመሰረተው አዲስ መንግስት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ የዕድገት ምዕራፍ በማሸጋገር ረገድ ትልቅ ኃላፊነት አለበት።

ኢትዮጵያን ማሻገር ለመንግስት ብቻ የሚተው ጉዳይ አለመሆኑን ጠቅሶ፤ ኢትዮጵያዊያን የጀመሩትን አንድነት በማጠናከር የሚመሰረተውን መንግስት ማገዝ ይጠበቅባቸዋል ነው ያለው።

ሕዝቡ ምን እና ማን እንደሚበጀው ለይቶ አውቋል ያለው አትሌት ሻለቃ ሃይሌ፤ በመሆኑም ይህን ተገንዝበን እጅ ለእጅ ተያይዘን በመስራት አገራችንን መለወጥ አለብን ብሏል።

መንግስት በበኩሉ እስከታችኛው መዋቅር ሕዝብ የማገልገል ብቃትና ታማኝነት ያላቸውን አመራሮች ወደ ሃላፊነት ማምጣት እንዳለበት ነው የተናገረው።

በመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገቡ አመራሮች ኢትዮጵያ ከገጠሟት ችግሮች እንድትላቀቅ የሚሰሩ መሆን እንዳለባቸውም ጠቁሟል።

ኢትዮጵያን የሚያግዙ ወዳጅ አገሮች እንዳሉ ሁሉ ህልውናዋን የማይፈልጉት አዲስ የሚመሰረተው መንግስት እንዳይጸና የተለያዩ ሴራዎችን ሊያሴሩ እንደሚችሉም ገልጿል።

ነገር ግን ለኢትዮጵያ ህልውና መጠበቅና መልማት ዋነኞቹ ባለጉዳዮች የውጭ ሃይሎች ሳይሆኑ ኢትዮጵያዊያን መሆናቸውን ተናግሯል።

"ኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞዋን ጀምራለች" ያለው ሻለቃ ሃይሌ ገብረስላሴ፤ የከፍታ ጉዞ ሲጀመር ፈተናዎች ማጋጠማቸው የሚጠበቅ ጉዳይ ነው ብሏል።

በመሆኑም ፈተናዎችን በመጋፈጥ ኢትዮጵያን ከከፍታው አናት ላይ ማስቀመጥ እንደሚገባ አመልክቷል።

ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ አህመድ የምርጫውን ሂደት አስመልክተው ባስተላለፉት መልዕክት "በምርጫው ኢትዮጵያ አሸንፋለች፤ ይህ እውን የሆነው ደግሞ መንግስትና በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች አገራቸውን አስቀድመው በመስራታቸው ነው" ሲሉ መናገራቸው ይታወሳል።

ፓርቲያቸው በሚያዋቅረው አዲሱ መንግስት በምርጫው የተሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንደተሳትፏቸው መጠን ከታችኛው የመንግስት መዋቅር ጀምሮ በመንግስት አደረጃጀት ውስጥ እንደሚካተቱ መግለጻቸውም አይዘነጋም።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም