ቀጥታ፡

ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን የሚጠናክሩበት ነው

አዲስ አበባ መስከረም 15/2014 (ኢዜአ) ኢትዮጵያዊያን ከመቼውም ጊዜ በላይ አንድነታቸውን የሚጠናክሩበት ነው ሲሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ ተናገሩ።

የአዲስ አበባ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ከአዲስ አበባ ደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር ኤጀንሲ ጋር በመተባበር የደመራ በዓል የሚከበርበትን የመስቀል አደባባይ አጽድቷል።

ከተለያዩ እምነት ተቋማት የተውጣጡ አባቶችና ተወካዮች ከበጎ ፍቃደኛ ወጣቶች ጋር በመተባበር ነው ፅዳቱን ያከናወኑት።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የማዘጋጃ ቤታዊ ዘርፍ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ የዘንድሮው የደመራ በዓል ባማረ መልኩ በታደሰው የመስቀል አደባባይ መከበሩ ልዩ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።

የመስቀል ደመራ በዓል ከኢትዮጵያዊያን አልፎ የዓለም ሆኗል ያሉት አቶ ጥራቱ በዓሉ ፍቅር፣ አንድነትና ወንድማማችነት የሚንጸባረቅበት እንደሆነም አንስተዋል።            

በዓሉ በሠላም እንዲከበር የሁሉም አካላት ርብርብ ወሳኝ በመሆኑ የሁላችንም የቤት ሥራ ሊሆን ይገባልም ብለዋል።

የአዲስ አበባ መካነ ሰማዕት ቅዱስ ቂርቆስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ መልዓከ ጸኃይ በቀለ ተሰማ የመስቀል በዓል የኦርቶዶክስ ቢሆንም የሌሎች እምነት ተከታዮች ቦታውን በማጽዳታቸው ቤተክርስቲያን ደስ ተሰኝታለች ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንም ከዚህ ቀደም በመሰል ፅዳት ተሳትፋለች ያሉት አስተዳዳሪው ይህን መሰል ትብብሮች የኢትዮጵያ ውበት መገለጫዎች በመሆናቸው ሊጠናከሩ ይገባል ብለዋል።

የደብረ ሠላም ቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ-ክርስቲያን ዋና አስተዳዳሪ ሊቀ መምህራን ለይኩን አያሌው በበኩላቸው ኢትዮጵያዊያን የሚያምርብን ስንተባበር ነው ብለዋል።

የተገበርነው "ድር ቢያብር አንበሳ ያስር" የሚለውን ብሂል ነው ያሉት ከአዲስ አበባ የኃይማኖት ተቋማት ጉባኤ የተወከሉት አብዱላዚዝ ወጉ 'ይህ ሥራን ያቀላለል፤ የትብብር መንፈስን ያጎልብታል' ብለዋል።  

በዓለም የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ የተካተተው የመስቀል ደመራ በዓል ነገ መስከረም 16 ቀን፤ መስከረም 17 ደግሞ የመስቀል በዓል ይከበራሉ።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም