ለአገር አንድነትና ለህዝብ ህልውና የሚከፈል መስዋዕትነት ዋጋው ከፍ ያለ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ለአገር አንድነትና ለህዝብ ህልውና የሚከፈል መስዋዕትነት ዋጋው ከፍ ያለ ነው
ባህር ዳር፣ መስከረም 15 ቀን 2014 (ኢዜአ) ''ለአገር አንድነትና ለህዝብ ህልውና ሲባል የሚከፈል መስዋዕትነት በታሪክ ትልቅ ስፍራ የሚሰጠው የጀግንነት ተጋድሎ ነው'' ሲሉ ባለሀብቱ አቶ ወርቁ አይተነው ተናገሩ፡፡
ባለሃብቱ በጎንደር ከተማ የአሸባሪውን የህወሃት ቡድን ወረራ ለመቀልበስ በግንባር ሲፋለሙ መስዋዕት ለሆኑ ጀግኖች ቤተሰቦች የአንድ ሚሊዮን ብር ድጋፍ ትናንት ማምሻውንባደረጉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ አገር ለማዳን ሲፋለሙ መስዋእት የሆኑ ጀግኖች ምንጊዜም ሕያው ናቸው።
አሸባሪው ህወሃት በፈጸመው ወረራ ያደረሰው ጥፋትና ውድመት በርካታ ወገኖችን ማፈናቀሉን ገልጸው፤ “ለወገን ደራሽ ወገን በመሆኑ ካለን በማካፈል ልንደርስላቸው የሚገባው ጊዜ አሁን ነው” ብለዋል።
“ከግል ሀብትና ምቾት የሀአገርና የህዝብ ክብርና አንድነት ይቀድማል” ያሉት አቶ ወርቁ አይተነው፤ ወገንን ለመታደግ ዛሬም ሆነ ነገ ያላቸውን በመስጠት በችግሩ ጊዜ ደራሽ በመሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ አረጋግጠዋል።
“ባለሀብቶች ለህልውና ዘመቻውም ሆነ በወረራው ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን እስከ አሁን ከ500 ሚሊዮን ብር በላይ አዋጥተን በማሰባሰብ ድጋፍ አድርገናል” ሲሉም ገልጸዋል፡፡
የጎንደር ከተማ ከንቲባ አቶ ሞላ መልካሙ በበኩላቸው የአሸባሪው ህወሃት ወረራ ኢትዮጵያውያንን ወደ አንድነት ያመጣ የታሪክ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።
ባለሀብቱ በጎንደር ከተማ በመገኘት ወረራውን ለመቀልበስ በግንባር ሲፋለሙ መስዋእት ለሆኑ ጀግኖች ቤተሰቦች ላደረጉት ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
ወንድማቸው ወራሪውን ሲፋለም መስዋእት የሆነባቸው አቶ ገበየሁ እንየው “ወንድሜ ለአገር አንድነትና ሉአላዊነት በከፈለው መስዋዕትነት ታላቅ ክብር ይሰማኝል፤ ባለሀብቱ ባደረጉት ወገናዊ ድጋፍም ተደስቻለሁ” ብለዋል፡፡
''ባላቤቴ አገር አፍራሹን የሽብር ቡድን ሲፋለም መስዋእት መሆኑ የክብር ሞት ነው'' ያሉት ደግሞ በፍልሚያው የትዳር አጋራቸውን ያጡት ወይዘሮ ፍቅሬ ሽመካች ናቸው፡፡
“ባለሀብቱመስዋእት የሆኑ ቤተሰቦችን በማስታወስ ላደረጉት ድጋፍ ምስጋናና አክብሮት አለኝ” ብለዋል።