ቀጥታ፡

መራጩ ህብረተሰብ ድምጹን ላመነበት ፓርቲ በመስጠት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለበት

መስከረም 14 ቀን 2014 (ኢዜአ)በሐረሪ ክልል በቅርቡ በሚካሄደው ምርጫ መራጩ ህብረተሰብ ድምጹን ላመነበት ፓርቲ በመስጠት የነቃ ተሳትፎ ማድረግ አለበት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ ገለጹ።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ የጀጎል ልዩና የመደበኛ ምርጫ ክልሎች የምርጫ ቅስቀሳ ማጠናቀቂያ መድረክ ዛሬ ሐረር ላይ ተካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የፓርቲው ከፍተኛ አመራሮች፣የፓርቲው ዕጩዎች፣ በሐረሪ ክልልና ከክልሉ ውጭ የሚኖሩ የብሔረሰቡ አባላትና የክልሉ ነዋሪዎች እንዲሁም እንግዶች ተገኝተዋል።

ርዕሰ-መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት እንዳመለከቱት በቀጣዩ ሳምንት በሚካሄደው ምርጫ ለመራጭነት የሚያበቃ የምርጫ ካርድ የወሰዱ ሁሉ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ጠይቀዋል።

አቶ ኦርዲን ነዋሪዎች በምጫው ላይ ድምጻቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።ከክልሉ ውጪ የሚገኙ የብሔረሰቡ አባላት የምርጫ ካርድ እንዲወስዱ ላደረጉ አካላት በተለይም ለኦሮሚያ ክልል መንግሥትና ሕዝብ ምስጋና አቅርበዋል።

የወከሉት ብልፅግና ፓርቲ ከሁሉም ብሔሮችና ብሔረሰቦች ጋር ወንድማማችነትንና አብሮነትን በማጠናከር የአገሪቱን የብልፀግና ጉዞ ለማረጋገጥ እንደሚሰራም ተናግረዋል።

ሕዝቡ ድምፁን ከሰጠን የተሻለ ሥራ እንሰራለን፤ ለዚህም ቃል እንገባለን’’ ብለዋል አቶ ኦርዲን።

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ምርጫ ጽህፈት ቤት ኃላፊው አቶ አብዱልሃኪም ዑመር በበኩላቸው በክልሉ በመራጭነት የተመዘገበው ሕዝብ ከሚጠበቀው በላይ እንደነበር ተናግረዋል።

በምዝገባው የተሳተፈው ሕዝብ በድምፅ መስጫው ዕለት ፓርቲያቸውን በመምረጥም የአገሪቱን ብልፅግና እንዲያረጋግጥ ላቀዱት ስራ አጋር እንዲሆን ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ባለፈው ዓመት በተለያዩ ምክንያቶች ምርጫ ባልተከናወነባቸው ክልሎች መስከረም 20 ቀን 2014 ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት እያደረገ መሆኑ ይታወቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም