ቀጥታ፡

የወገኖቼን ደህንነት ለመጠበቅ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ወስኛለሁ

አሶሳ ፤ መስከረም 14 / 2014 (ኢዜአ)''የወገኖቼን ደህንነት ለመጠበቅ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ወስኛለሁ'' የምትለዋ ወጣት ሂጂራ አደም ናት።

ሂጂራ በፈቃዳቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ከወሰኑ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ወጣቶች አንዷ ናት፡፡

በክልሉ በሁለተኛ ዙር በፈቃዳቸው መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ከወሰኑ ወጣቶች ትናንት በአሶሳ ሽኝት ተደርጎለታል፤ በግልገል በለስ ተመሳሳይ  መረሃ ግብር ተካሄዷል።

የማኦ ኮሞ ልዩ ወረዳ ነዋሪ ሂጂራ ጀግናውን መከላከያ ሠራዊት ለመቀላቀል በመወሰኗ  ደስተኛ እንደሆነች ነው የተናገረችው፡፡

ሽብርተኛው ህወሃት ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ሲጥር ተላላኪው ሸኔ ደግሞ የአካባቢዋን ነዋሪዎች ሠላም እንደሚነሳ በቁጭት ትገልጻለች።

''የጥፋት ቡድኑ በሕዝብ ላይ የሚደርሰው ጥቃት ያንገበግበኛል'' ስትልም ታክላለች፡፡

''የወገኖቼን ደህንነት ለመጠበቅ በማሰብ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል ወስኛለሁ''በማለትም ወጣቷ ለኢዜአ አስተያየቷን ሰጥታለች፡፡

ወጣቱ   እንደ እሷ ሀገሩን ለማዳን እንዲዘምትም ሂጂራ ምልዕክት አስተላልፋለች፡፡

ሽብርተኛው ህወሃት ሀገርን የማጥፋት ግቡን ለማስፈጸም ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልን ማዕከል አድርጓል የሚለው ደግሞ ወጣት ረቢ አደም ነው፡፡

እርሱ በሚኖርበት አሶሳ ዞን ኦዳቢልድግሉ ወረዳ የሽብርተኛው ህወሃት ጥፋት አስፈጻሚ ቡድን ንጹሃን ሽማግሌዎችንና ህጻናትን ሳይቀር መግደሉን ይገልጻል፡፡

የሀገር መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀል በኢትዮጵያ ላይ የተቃጣውንና በአካባቢው ጥፋት እያደረሰ ያለውን  አሸባሪ ቡድን ለማስወገድ መነሳቱን የሚናገረው ቁጭት በተላበሰ መንፈስ ነው፡፡

“እኛ ወጣቶች እያለን ኢትዮጵያን ማፍረስ አይቻልም” ሲልም የእሱንና የዕድሜ እኩዮቹን አቋም አንጸባርቋል።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ሃላፊ አቶ ሙሳ ሐሚድ  ፤ወጣቶቹ  ኢትዮጵያን ለውጭ ኃይሎች አሳልፎ ለመስጠት ጭምር የሚንቀሳቀሰውን ቡድን ለመደምሰስ የሀገር መከላከያ ሠራዊትን ለመቀላቀል በመወሰናቸሁ ደስተኛ ነኝ ብለዋል፡፡

መሠረቱን ሕዝብ ያደረገውን መከላከያ ሠራዊት በመቀላቀል እንደ አባቶቻችን ጠላትን እንደሚያሳፍሩም እምነታቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

''ኢትዮጵያ ከእናንተ የምትጠብቀው በእውቀት የታነጸ ወታደር እንድትሆኑ ነው'' ብለዋል፡፡

በሀገር መከላከያ ሚኒስቴር የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይዘን ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ታዬ ቶሎሳ በበኩላቸው፤ ሠራዊቱ የጦር ጀግኖችን ብቻ ሳይሆን የበርካታ ሙያ ባለቤት የሆኑ ኢትዮጵያውያንን የሚያፈራ ተቋም እንደሆነ ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ሕዝብ ልዩ ፍቅርና ክብር የሰጠውን ሠራዊት መቀላቀል እንደሚያኮራና በሥነ ምግባር ታንጾ ለመውጣት እንደሚያስችል አስረድተዋል፡፡

በውትድርና ሙያ ውስጥ ሆነው ሀገራቸውን ከሽብርተኛው ህወሃት ጥፋት ከማዳን በተጨማሪ ራዕያቸውን ማሳካት እንደሚችሉ ኮሎኔል ታዬ ለወጣቶቹ ገልጸዋል፡፡

የክልሉ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ አባላት ለወጣቶቹ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በማስረከብ ሀገራቸው በሽብርተኛው ህወሃት የተደቀነባት ፈተና እንዲመክቱ አደራ ሰጥተዋል፡፡

በክልሉ ባለፈው ዓመት በርካታ ወጣቶች የሀገር መከላከያ ሠራዊት መቀላቀላቸውን በወቅቱ ተዘግቧል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም