የባንክ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አጥተው መጉላላት እንደገጠማቸው በጂግጂጋ ከተማ ተገልጋዩች ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
የባንክ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ አጥተው መጉላላት እንደገጠማቸው በጂግጂጋ ከተማ ተገልጋዩች ገለጹ
ጂግጂጋ ነሀሴ 9/2010 በጂግጂጋ ከተማ አብዛኛዎቹ ባንኮች ባለመከፈታቸው በቂ አገልግሎት በማጣት እየተጉላሉ መሆናቸውን በከተማዋ አገልገሎቱን ፈላጊ ነዋሪዎች ገለጹ፡፡ ከተገልጋችዮ መካከል አቶ መሐመድ አብዲ በሰጡት አስተያየት በአሁኑ ወቅት በጅግጅጋ ከተማ መረጋጋት ተፈጥሮ አንፃራዊ ሰላም መስፈኑን ተናግረዋል፡፡ ሆኖም ከአገልግሎት ሰጪ ተቋማት መካከል ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በስተቀር የግል ባንኮች ስራቸውን ባለመጀመራቸው መቸገራቸውን ገልጸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ በጀግጅጋ ከተማ ካሉት ሰባት ቅርንጫፎች አገልገሎት የሚሰጡት ሁለት ብቻ መሆናቸውን ያመለከቱት ደግሞ አቶ ሙህዲን ሼህ አብርአህማን የተባሉት የከተማው ነዋሪ ናቸው፡፡ በዚህም ምክንያት አገልግሎት ለማግኘት በአንድ መስኮት በተፈጠረው መጨናነቅ መጉላላት እየገጠማቸው በችግር ላይ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ውስን በሆኑት የንግድ ባንኮች ተገልጋዮች ረጃጅም ሰልፍ ይዘው ለሰዓታት መጠበቅ ግዴታ ሆኖባቸዋል። በከተማው የባንክ አገልገሎት ለማግኘት ሲባል ስራዎቻቸውን ትተው ጊዜያቸው ተራ በመጠበቅ እያሳለፉ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር እየገጠማቸው መሆኑን አስተያየት ሰጪዎቹ ተናግረዋል፡፡ አቲኤም እንኳን በአግባቡ ባለመስራቱ ከመሰለፍ ውጭ አማራጭ ማጣታቸውን ጠቁመዋል። በከተማው አሁን ሰላምና መረጋጋት በመፈጠሩ ስራቸውን ያልጀመሩ ባንኮች ተከፍተው የተለመደውን አገልገሎት እንዲሰጧቸው የሚፈልጉ መሆናቸውን ተገልጋዮቹ አመልክተዋል። በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የጅግጅጋ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ አቶ ግርማ አየለ ስለጉዳዩ ተጠይቀው በሰጡት ችግሩ በሁከቱ ምክንያት የባንኩ ሰራተኞች ለጊዜው ከአካባቢ በመሸሻቸው የተፈጠረ ክፍተት መሆኑን ገልጸዋል። ባንኩ ይህን አገልግሎት እየሰጠ ያለውም በማህበረሰቡ ድጋፍ በቆዩ ሰራተኞች መሆኑን ጠቁመው ፤ በቀጣይ ከድሬዳዋ ዲስትሪክት ጋር በመነጋገር ሰራተኞች የሚመለሱበት ሁኔታ እንደሚመቻች ጠቁመዋል።