የድሬዳዋንና የምስራቅ ኢትዮጵያን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ እናስጠብቃለን - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋንና የምስራቅ ኢትዮጵያን ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ እናስጠብቃለን
ድሬዳዋ መስከረም 14/2014(ኢዜአ) የድሬዳዋንና የምስራቅ የአገሪቱን ክፍል ሰላምና ፀጥታ በአስተማማኝ መንገድ በመጠበቅ ሙያዊ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ የድሬዳዋ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነርና አባላት ተናገሩ።
ኮሚሽኑ ለ250 አባላትና አመራሮች የማዕረግ ዕድገት ሰጥቷል፡፡
ከረዳት ሳጅን ጀምሮ እስከ ኢንስፔክተርነት የማዕረግ ዕድገት የተሰጣቸውና ማዕረጉን የለበሱት በሥራ አፈጻጸማቸው የላቀ ውጤት ያመጡ ናቸው፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ኮሚሽነር ዓለሙ መግራ የኮሚሽኑ አመራሮችና አባላት የድሬዳዋንና የምሥራቅ ኢትዮጵያን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ለማድረግ በመስራት ላይ ናቸው።
ከተማዋ ያላትን ስትራቴጂክ አቀማመጥ መሠረት በማድረግ ከአካባቢው የፍትህና ፀጥታ አካላት ጋር በመቀናጀት የአገሪቱ የገቢና ወጪ ንግድ እንቅስቃሴ ሰላማዊ ሆኖ እንዲቀጥል ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል፡፡
የአስተዳደሩ ልዩ ኃይል አሸባሪው ህወሓትን ለመዋጋት ወደ ግንባር በመዝመት ከጸጥታ ኃይሎች በመቀናጀት በመሰለፍ አገር የማዳን ኃላፊነቱን እንሚያጠናክርም ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
''የማዕረግ ዕድገቱ እነዚህን ሥራዎች ይበልጥ በውጤት ለማጀብ ያግዛል'' ብለዋል፡፡
ከምክትል ኢንስፔክተርነት ወደ ኢንስፔክተርነት ያደጉት ዝናሽ በቀለ የአስተዳደሩንና የአጎራባች አካባቢዎች ሰላም ፀጥታ በመጠበቅ ኃላፊነታቸውን እንደሚወጡ ተናግረዋል።
አስፈላጊ ከሆነም በአገር በማዳን ዘመቻው እንደሚሳተፉ ገልጸዋል፡፡
ከረዳት ኢንስፔክተር ወደ ምክትል ኢንስፔክተር ያደጉት ባንተአለም ግርማ በበኩላቸው የማዕረግ ዕድገቱ የሕዝብና የአገር ታላቅ ኃላፊነት መሸከም በመሆኑ ኃላፊነቱን ለመወጣት ዝግጁ መሆናቸው አስታውቀዋል፡፡
''በፖሊስ ሙያዬም ሆነ በኮሚሽኑ ሚዲያ ላይ ያካበትኩት ዕውቀት አገርን በማዳን ዘመቻው ላይ ለማዋል ዝግጁ ሆኜ እየጠበቅኩ ነው'' ብለዋል፡፡
በምከትል ከንቲባ ማዕረግ የድሬዳዋ ንግድ ኢንዱስትሪና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊና የድሬዳዋ የፀጥታ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ከድር ጁሃር በአስተዳደሩና በአካባቢው አስተማማኝ ሰላምና ፀጥታ የማስፈን ሥራ እንዲያጠናክሩ አሳስበዋል፡፡
ለፖሊስ አመራርና አባላት ማዕረጉን የሰጡትና ያለበሱት የድሬዳዋ አስተዳደርና የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች ናቸው፡፡