ድርጅቱ ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ ዋና መስሪያ ቤት ሊያስገነባ ነው

90

መስከረም 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ከሁለት ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ዋና መስሪያ ቤት ለማስገንባት ግንባታውን ከሚያካሂድ ድርጅት ጋር ተፈራረመ።

ስምምነቱን የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈፃሚ ወይዘሮ የሺመቤት ነጋሽ እና የአሴፍ ኢንጅነሪንግ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አስራት ኤፍሬም ተፈራርመዋል።

በሜክሲኮ ገነት ሆቴል አካባቢ የሚገነባው ህንጻ ከመሬት በታች 4 እና ባለ 18 ወለሎች ያሉት ሲሆን፤ በሁለት ዓመታት ጊዜ ውስጥ ግንባታው እንደሚጠናቀቅ ተገልጿል።

የአማካሪነቱን ሥራ ቢኮን ኢንጅነሪንግ ያከናውነዋል።

የድርጅቱ ዋና ስራ አስፈጻሚ ወይዘሮ የሺመቤት እንደተናገሩት፤ ሕንጻው የተለያዩ ሱቆች፣ አዳራሾች፣ ሞሎች እና የተሽከርካሪ ማቆሚያ ስፍራ ይኖረዋል።

ህንጻው ተገንብቶ ለአገልግሎት ክፍት ሲሆን፤ የድርጅቱን ሥራ ዘመናዊ በማድረግ በኩል የራሱ ድርሻ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

የህንጻ ግንባታውን የሚያከናውነው የአሴፍ ኢንጅነሪንግ ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር አስራት ኤፍሬም በበኩላቸው ግንባታውን በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ለማጠናቀቅ ቃል ገብተዋል።

ድርጅቱ አገር በቀል ደረጃ አንድ ተቋራጭ መሆኑን ጠቅሰው፤ በአገሪቷ ትላልቅ ግንባታዎች ላይ ልምድ እንዳለው ጠቁመዋል።

"በቂ ማሽነሪና በቂ የሰው ሃይል ለዚህ ፕሮጀክት ዝግጁ አድርገን ወደ ግንባታ ለመግባት ተዘጋጅተናል" ብለዋል።

የኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ግብዓቶች ልማት ድርጅት ከዚህ በፊት ጅንአድ በመባል የሚታወቅ ሲሆን፤ በመላው ኢትዮጵያ 83 ቅርንጫፎች አሉት።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም