"የአሁኑ ወቅት ሁላችንም ለመትረፍ የምንረባረብበት እንጂ ለማትረፍ የምንሮጥበት አይደለም" - አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ - ኢዜአ አማርኛ
"የአሁኑ ወቅት ሁላችንም ለመትረፍ የምንረባረብበት እንጂ ለማትረፍ የምንሮጥበት አይደለም" - አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ
መስከረም 14/2014 (ኢዜአ)"የአሁኑ ወቅት ሁላችንም ለመትረፍ የምንረባረብበት እንጂ ለማትረፍ የምንሮጥበት አይደለም" ሲል የሰዎች ለሰዎች ድርጅቱ የክብር አምባሳደር አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ ተናገረ።
ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከሰሜን ወሎ ተፈናቅለው ደሴ ከተማ ለሚገኙ ወገኖች ከ 12 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ድጋፍ አደርጓል።
ላለፉት 40 ዓመታት በአገሪቷ የተለያዩ የልማት ስራዎችን በማከናወን ላይ የሚገኘው ሰዎች ለሰዎች ድርጅት በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ከመኖሪያ ቀዬአቸው የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማገዝ ድጋፍ አድርጓል፡፡
በድጋፍ አሰጣጡ ላይ የተገኘው የድርጅቱ የክብር አምባሳደር አትሌት ሻለቃ ኃይሌ ገብረስላሴ፤ ወቅቱ "ሁላችንም ለመትረፍ የምንረባረብበት እንጂ ለማትረፍ የምንሮጥበት አይደለም" ሲል ተናግሯል፡፡
የሰዎች ለሰዎች ድርጅት ባለፉት 40 ዓመታት በአገሪቷ የተለያዩ የልማት ስራዎችን ማከናወኑንም አስታውሷል፡፡
የተፈጠረውን ችግር ለመሻገር "ሰው መኖር አለበት ሰው እንዲኖር ደግሞ ሁላችንም መረባረብ አለብን" በማለት ነው የገለጸው አትሌት ኃይሌ ገብረስላሴ፡፡
ከዚህ ባለፈ ጦርነት በተካሄደባቸው አካባቢዎች ያሉትን ተፈናቃይ ወገኖቻችንን አቋቁመን ወደ ቀደመ ቀዬአቸው ለመመለስ እርብርብ እንዲደረግ ጠይቋል፡፡
ድርጅቱ ከዚህ የበለጠ ችግር የለም በማለት ከሰሜን ወሎ ዞን በአሸባሪው ህወሃት ወረራ ለተፈናቀሉ ዜጎች ድጋፍ ማድረጉን ገልጿል፡፡
በአሸባሪው ህወሃት ምክንያት ተፈናቅለው በተለያዩ ቦታዎች ተጠልለው የሚገኙ ወገኖችን "ከጎናችሁ ቆመናል" ሲል ባጋጠማቸው ጊዜያዊ ችግር ስጋት እንዳይገባቸው መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡
የሰዎች ለሰዎች ድርጅት የኢትዮጵያ ተጠሪ አቶ ይልማ ሃይሌ በዚሁ ወቅት፤ ድርጅቱ በጦርነቱ ምክንያት ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍ ከ12 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የተለያዩ ቁሳቁሶችን በድጋፍ መስጠቱን ተናግረዋል ፡፡
ድርጅቱ የተፈጠረውን ችግር አይቶ በሚችለው አቅም ድጋፍ ለማድረግ መነሳሳቱንም ጨምረው ገልጸዋል፡፡
በድጋፍ አሰጣጡ ሂደት በቦታው ያለው ችግር የከፋ መሆኑን መገንዘባቸውን በመናገር ሌሎችም የድርጅቱን አርዓያ በመከተል ድጋፍ እዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የደቡብ ወሎ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ሰይፉ ሰዒድ በበኩላቸው፤ የተፈናቃዮቹን ፍላጎት በመንግስት እገዛ ብቻ መሙላት ስለማይቻል ሁሉም ድጋፉን እንዲቀላቀል ጠይቀዋል፡፡
በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች "እኔም ለወገኔ አለሁ" በማለት እያደረጉ ላለው ድጋፍ ምስጋና እቅርበዋል፡፡
የሰዎች ለሰዎች ድርጅት በዞኑ ባለፉት 40 አመታት ህብረተሰቡን በስፋት ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ የልማት ተግባራት ማከናወኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ትምህርት ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ ክሊኒኮችንና የጉድጓድ ውኃዎችን በማውጣት በርካታ ህዝቦችን ተጠቃሚ ማድረጉንም ተናግረዋል፡፡