ቀጥታ፡

የአሜሪካ መንግስት ጫና ለሰብአዊ መብት ተቆረቁሮ ሳይሆን ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር ነው - አቶ ኦባንግ ሜቶ

ጋምቤላ፣ መስከረም 14 ቀን 2014 (ኢዜአ) የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየጣረ ያለው ለሰብአዊ መብት ተቆረቁሮ ሳይሆን የራሱን ጥቅም የሚያሟላ ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር መሆኑን የሰብአዊ መብት ተማጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ አስታወቁ።

አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ጠንካራ ሆኖ የህዝቡን አንድነት በማጠናከር የውጭ ሃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር የሚያደርጉትን ሙከራ መቋቋም እንደሚቻልም አመልክተዋል።

የሰብአዊ መብት ተማጋቹ አቶ ኦባንግ ሜቶ ዛሬ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ የአሜሪካ መንግስት በሰብአዊ  መብት ሽፋን በኢትዮጵያን ላይ ጫና ለመፍጠር እያደረገ ያለው ሂደት ተገቢ አይደለም።

ኢትዮጵያ ሉዓላዊነት ያላት ሀገርና የራሷን ችግር በራሷ የመፍታት መብትና አቅም እንዳላት አስገንዝበዋል።

የአሜሪካ መንግስት የሰብአዊ መብት ጥሰት እያደረሰ ያለውን የህወሐት የሽብር ቡድን አይቶ እንዳላያ ዝም በማለት በመንግስት ላይ ጫና እየፈጠረ ያለው ለጥቅሙ ሲል መሆኑን አስረድተዋል።

"በተለይም የህወሓት የሽብር ቡድን እየፈጸማቸው ስላሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምንም ነገር የማይለው የራሱን ጥቅም የሚያሟላ ተላላኪ መንግስት ለመፍጠር በማሰብ ነው" ብለዋል።

"የአሜሪካ መንግስት ለሰብአዊ መብት ቢያሰብ ኑሮ የሽብር ቡድኑ በአማራና አፋር ክልሎች በዜጎች ላይ ስለፈጸማቸው ግፍና በደሎች በዝምታ ባላለፈ ነበር" ሲሉ ገልጸዋል።

አንዳንድ ድርጅቶች በሰብአዊ እርዳታ ሽፋን የስለላ ስራና ጦር መሳሪያች ለሽብር ቡድኑ  የማቀበል ሁኔታዎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።

በቅርቡ የሚመሰረተው መንግስት ጠንካራ ከሆነ እና የኢትዮጵያ ህዝብ በአንድነት መቆም ከቻለ የአሜሪካም ሆነ የሌሎች ምዕራባውያን ሀገራት ዛቻና ማፈራራት የሚያመጣው አንዳችም ችግር እንደማይኖር ተናግረዋል።

የሽብር ቡድኑ ህጻናትን እና ሌሎች ሲቪል ሰዎችን በግድ ወደ ጦርነት በማሰለፉ በዓለም አቀፍ ህግጋት በወንጀል የሚያስጠይቅ ተግባር መሆኑንም አውስተዋል።

አሁን ላይ ግን ኢትዮጵያን በተመለከተ አሜሪካ እያራመደች ያለው ፖሊሲ የሁለቱን አገሮች ታሪካዊ ወዳጅነትን የሚቃረን መሆኑን አመልክተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም