የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ - ኢዜአ አማርኛ
የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ ተጠየቀ
መስከረም 13 ቀን 2014 (ኢዜአ) የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ህዝቡ የበኩሉን እንዲወጣ የሃይማኖት አባቶችና አባገዳወች ጠየቁ።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ "ክብረ በዓላችን ለሰላማችን" በሚል ከሃይማኖት አባቶች፣ አገር ሽማግሌዎችና አባገዳዎች ጋር የመስቀል እና ኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲከበሩ እየተደረጉ ባሉ ዝግጅቶች ላይ መክሯል።
በመድረኩ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን በመላ አገሪቷ የሚከበረው የመስቀል ደመራ እና የኦሮሞ ሕዝብ ለፈጣሪ ምስጋና የሚያቀርብበት የኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ የተደረጉ ዝግጅቶች ላይ ውይይት ተደርጓል።
ኢዜአ ያነጋገራቸው የሃይማኖት አባቶችና አባገዳ በዓላቱን ለማክበር የተደረጉ ዝግጅቶችን ዘርዝረዋል።
የአደባባይ በዓል ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ከአገር ውስጥና ከውጪ የሚገኙ ታዳሚዎች የበዓላቱን ሃይማኖታዊና ባህላዊ እሴት በሚያሳይ መልኩ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።
መስከረም 16 ቀን የሚከበረውን የደመራ በዓል ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር ከወጣቶች፣ ከጸጥታ አካላትና ከእምነቱ ተከታዮች ጋር በየአካባቢያቸው ማድረጋቸውን የሃይማኖት አባቶች ገልጸዋል።
በዓላቶቹ በተከታዮቻቸውና አማኞቻቸው ይለያዩ እንጂ የሁሉም ኢትዮጵያዊ በዓላት በመሆናቸው የተለያ እምነትና ባህል ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎችም በዝግጅቱ ላይ እንደሚሳተፉ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ ያላትን የእምነት፣ የባህልና አንድነት የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ወጣቶች፣ ሴቶችና ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የበኩላቸውን እንዲወጡ የሃይማኖት አባቶችና አባገዳዎች ጠይቀዋል።
የንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ተገኝ ድንቅነህ በበኩላቸው፤ የመስቀል ደመራና ኢሬቻ በዓላትን በሰላም ለማክበር ከወጣቶች፣ ሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎች ጋር ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ እምነት ተከታዮች ዘንድ የሚከበረው የመስቀል ደመራ በዓል መስከረም 16ና 17 የሚከበር ሲሆን፤ የኢሬቻ በዓል ደግሞ በአዲስ አበባ መስከረም 22 ቀን 2014 ዓ.ም ይከበራል።