አህጉራዊ ትብብር የፈጠረው ግድብ - ኢዜአ አማርኛ
አህጉራዊ ትብብር የፈጠረው ግድብ
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ለሀገራችን ፈተናዎችና መሰናክሎች የፈጠሩ ክስተቶች ብቅ ብቅ ማለታቸው በዓለም ጂኦፖለቲካዊ ገጽታ ላይ የራሳቸውን ጫና እያሳደሩ ይገኛሉ። በዚህ ረገድ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝን ያህል ተጽዕኖ የፈጠረ ክስተት ባይኖርም የአየር ንብረት ለውጥና የድንበር ተሻጋሪ ተፋሰሶች አጠቃቀም ከዚህ ባልተናነሰ መልኩ ጫና ፈጥረዋል።
በአንፃሩ እነዚህ ርዕሰ ጉዳዮች ከሚፈጥሯቸው አሉታዊ ጫናዎች ባሻገር የዘርፈ ብዙ ዓለም አቀፋዊ ትብብር አስፈላጊነትን ማጉላት የቻሉበት አዎንታዊ ዕድልም መፍጠር ችለዋል። አገራት በእነዚህና በሌሎች አዳዲስ ዓለም አቀፋዊ ጉዳዮች ተቀራርበውና በጋራ ተባብረው መስራት እንደሚኖርባቸው የማንቂያ ደወል ያህል ጠቃሚ ሆነዋል። ለማሳያ ያህል በቅርቡ ዓለማችንን የፈተነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ አገራት በትብብር መስራት እንዳለባቸው ያስገደደ ክስተት ሆኗል።
ከዓለም አቀፍ የውኃ ኃብት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ አለመግባባቶችና ግጭቶች በቀና የትብብር መንፈስ ሰላማዊ እልባት እንዲያገኙ ማድረግ የተቻለባቸው በርካታ አጋጣሚዎችም ተሰተውለዋል። በጋራ ድንበሮቻቸው ወንዞችንና ሀይቆችን የሚጋሩ አገራት አስማሚ የትብብር ማዕቀፍ በመፍጠር ከጋራ ትሩፋት አትራፊ መሆን የቻሉ አገራትም በርካታ ናቸው። እንደ ባንግላዴሽ፣ ቡህታን፣ ህንድ፣ ኔፓል እና ቻይና የመሳሰሉ አገራትም በታላቁ የጋንጀስ ወንዝ ተፋሰስ የፈጠሩት የትብብር ስምምነት ለዚህ ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
ወዲህ መለስ ስንል በአህጉራችን አፍሪካ ምዕራባዊ ክፍል ሴኔጋል፣ ጊኒ፣ ማሊ እና ሞሪታኒያ በሴኔጋል ወንዝ ተፋሰስ ላይ የፈጠሩት የትብብር ስምምነትም በድንበር ተሻጋሪ የውኃ ኃብት አጠቃቀም በዋቢነት የሚነገርለት ትብብር ነው። ትብብሩ ለወትሮው ድርቅና የዝናብ እጥረት የማይለየው የሳህል አካባቢን የሚያካልለው የሴኔጋል ተፋሰስ ተጋሪ አገራት ተጠቃሚነትን ባረጋገጠ መልኩ የተደረሰ ስምምነት ነው።
እነዚህ አገራት የሴኔጋል ወንዝ ተፋሰስ ልማት ድርጅት Senegal River Basin Development Organization (OMVS) በሚል የፈጠሩት የጋራ የትብብር ስምምነት በተፋሰሱ ዙሪያ ለዘመናት ይነሱ የነበሩ ግጭቶችንና አለመግባባቶችን ማስቀረት ችሏል። ከተዛባ የቅኝ ግዛት ውርስ ጋር በተያያዘ የናይል (አባይ) ተፋሰስ አገራትም በተፋሰሱ አጠቃቀም ዙሪያ ከእነዚህ አገራት ተሞክሮ ሊወስዱ ይገባል።
የናይል ተፋሰስ አገራት ከኢትዮጵያ በቀር ፈራ ተባ ከማለት በዘለለ ደፍረው ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ቀርጸው መንቀሳቀስ ሳይችሉ ቀርተዋል። ለዚህ ደግሞ በምክንያትነት የሚወሳው ግብጽና ሱዳን እ.ኤ.አ በ1929 እና በ1959 የተፈራረሟቸው ኢ-ፍትሃዊ የዓባይ ውሃ አጠቃቀም ስምምነቶች ናቸው። ስምምነቱ የተፋሰሱን አገራት የትብብር መንፈስ ከማጎልበት ይልቅ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ያደረገ ፍትሃዊ ተጠቃሚነትን ታሳቢ ያላደረገ ዘመኑ ያለበት ስምምነት ነው።
በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ ቀድሞም ጠንካራ እምነት በመያዝ የዓለም መንግሥታት ማህበርን ቀጥሎም የተባበሩት መንግሥታትና የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን መስራች የሆነችው ኢትዮጵያ በናይል ተፋሰስ ፍትሃዊ የውኃ አጠቃቀም እንዲረጋገጥ የሚያስችሉ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን እያደረገች ትገኛለች።
የናይል ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍን ከመፍጠር አንስቶ እስከ ታላቁ የህዳሴ ግድብ ፕሮጀክትን እውን እስከ ማድረግ የተኬዱት ርቀቶች የዚህ ማሳያዎች ናቸው። ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ለኢትዮጵያ፣ ለሱዳንና ግብጽ በተለየ መልኩ የትብብር እድል የሚፈጥር ስለመሆኑ በርካታ የጥናት ውጤቶች ይጠቁማሉ። ግድቡ በሚያመነጨው ግዙፍ የኤሌክትሪክ ሃይል መጠን የቀጠናውን የልማት እንቅስቃሴ በመለወጥ ረገድ እንዲሁም አካባቢውን በማስተሳሰር በኩል የጎላ ሚና እንዳለው እነዚሁ ጥናቶች ያስረዳሉ።
የህዳሴ ግድብ ግንባታ በብዙ ችግሮች ውስጥ ወደ ግንባታው መጠናቀቂያ ምዕራፍ ሲደርስ ማየት የቻሉት የቅርብና የሩቅ የተፋሰሱ አገራት ከግድቡ ትሩፋት ለመቋደስ የኢትዮጵያን በር ማንኳኳት ከጀመሩ ሰነባብተዋል። ይህ ደግሞ በተፋሰሱ የልማት ፕሮጀክቶች ዙሪያ የትብብር መንፈስ እንዲጎለብት የህዳሴውን እርሾ እየሆነ ይገኛል። ግድቡ ከመነሻው አንስቶ አሁን እስከ ደረሰበት ደረጃ ግንባታውን ስትቃወም የነበረችውን ሱዳን እንኳ የዚህን ትሩፋት ቀዳሚ ተጋሪ ለመሆን ሰፊ ጥረት እያደረገች ትገኛለች።
ቀደም ሲል ሱዳን ከኢትዮጵያ ስትወስደው ከነበረው 200 ሜጋ ዋት የሚጠጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ለህዝቧ በቂ አለመሆኑን በመገንዘብ ተጨማሪ የኃይል አቅርቦት ጠይቃለች። አሁን ላይ ሱዳን አንድ ሺህ ሜጋ ዋት የኃይል አቅርቦት ከኢትዮጵያ መግዛት እንደምትፈልግ በኢነርጂና ነዳጅ ሚኒስትሯ ጄደን ዓሊ ኦቢድ በኩል ይፋ ማድረጓ የቀደመው አቋሟ ዳግም እንድታጤን የሚያደርግ መሆኑን ያመለካተ ጉዳይ ሆኗል። ይህን ተከትሎ ባለፈው ወር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ባለሥልጣን ከፍተኛ ባለሙያዎች ወደ ካርቱም አቅንተው የኤሌክትሪክ መስመር ለመዘርጋትና ተያያዥ ሥራዎችን ለማጠናቀቅ የሚያስችል የግንባታ ጥናት ማድረግ ችለዋል። ይህም አገራት ለህዝቦቻቸውን ጥቅምና የጋራ ብልጽግና ትብብር አማራጭ የሌለው ጉዳይ እንደሆነ የሚያሳይ ነው።
በተመሳሳይ ኬንያ ከኢትዮጵያ ለምትገዛው የኤሌትሪክ ኃይል አቅርቦት 500 ኪሎ ዋት መሸከም የሚችል ማስተላለፊያ መስመር ዝርጋታ ሥራ እየተጠናቀቀ ይገኛል። ቀሪ ሥራዎችን ማጠናቀቅ በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያም በኬንያው የኢነርጂና ነዳጅ ሚኒስትር ቻርለስ ኬተር የአገሪቱ ፓርላማ አባላት ልዑክ ከውኃ፣ መስኖ እና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶክተር ስለሺ በቀለ ጋር በጥልቀት መክረዋል።
ኢትዮጵያ ከኬንያ አልፎ በታንዛኒያ በኩል እስከ ደቡብ አፍሪካ የሚደርስ የ 2 ሺህ ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ኃይል ለማድረስ መታቀዱ የናይል ትብብር ከተፋሰሱ አገራት አልፎ አሕጉራዊ መልክ እንዲይዝ ያደርገዋል። ይህ ደግሞ ቀጣናዊ ውህደትን ከማቀላጠፍ አለፎ አፍሪካውያን ገቢራዊ ለማድረግ የደረሰቡትን አሕጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጣና (African Continental Free Trade Area-AfCFTA) እንዲጠናከር የሚያደርግ ነው።
በጋራ ዋኝቶ ውቅያኖሱን ማቋረጥ አሊያም አንድ ላይ መስመጥ የሚል አማራጭ የቀረበላቸው ከላይ የተጠቀሱት የእስያ ሆኑ የምዕራብ አፍሪካዎቹ የሴኔጋል ወንዝ ተጋሪ አገራት ልምድ የሚመሰክረው ትብብር አማራጭ የሌለው ጉዳይ መሆኑን ነው። እነዚህ አገራት ባጎለበቱት የትብብር መንፈስ የተፋሰሱን ውኃ ያለ አንዳች ኮሽታ አልምተው መጠቀም ችለዋል። እናም የናይል ተፋሰስ አገራት ልምድ ይቅሰሙ ሲባል በምክንያት እንደሆነ መገንዘብ ያሻል። በተላይ የቅኝ አገዛዝ ውልን እንደ አሳሪ ሕግ አድርገው የሚውስዱት ግብጽና ሱዳን አቋማቸውን በእንዲህ ዓይነቱ የትብብር መንፈስ ዳግሞ የመቃኛ ጊዜ አሁን ሊሆን ነው።
የህዳሴው ግድብ ግንባታ ለፖለቲካዊ ፍጃታነት ለማዋል መታተራቸው ተገቢ አለመሆኑን ዓለም ተግንዝቦታል። ከዚህ ይልቅ ግድቡ የሚፈጥረው ኢኮኖሚያዊ ትስስር የጎላ መሆኑን ተረድተው ዳግም ወደ አፍሪካዊ የትብብር ማዕቀፍ ሊመለሱ ይገባል።