የወጋ ቢረሳ …የተወጋ አይረሳም - ኢዜአ አማርኛ
የወጋ ቢረሳ …የተወጋ አይረሳም
አሸባሪው ህወሃት ተወልዶ እስከጎለመሰበት እንዲሁም አሁን የግብዓተ መሬቱ መፈጸሚያ ዋዜማ ላይ እስከደረሰበት ጊዜ ድረስ ዘወትር የሚያንጸባርቀው አንድ አመል አለው። ሲመቸው ህዝብን ማሰቃየትና ለመከራ መዳረግ፤ ስጋት ላይ ሲወድቅ ደግሞ ህዝብን መሸሸጊያ ጥላ የማድረግ የራስ ወዳድነት አመል መገለጫው ነው።
አሸባሪው ህወሓት በአፋር ህዝብ ላይ ያደረሰው ጭፍጨፋ ውሎ ሳያድር ዘንግቶት “የትግራይ ህዝብና የአፋር ህዝብ ለረጅም ጊዜ ተዛምዶ የኖረ ነው” በሚል ለማስረዳት ይሞክሯል። ቡድኑ በአፋር ክልል በፈጸመው ወረራ በጋሊኮማ እና ፈንቲ ረሱ አካባቢዎች በንፁሐን ላይ ያደረሰው ዘግናኝ ጭፍጨፋ ታሪክ የሚረሳው አይደለም። የሽብር ቡድኑ በአፋር ህዝብ፣ በመከላከያ ሠራዊት፣ በልዩ ሀይል እና ሚሊሻ የገጠመውን ሽንፈት ለመሸፋፈን በህዝብ ስም ነጋዴ ሆኖ ቀርቧል። ይህ ቡድን በአፋር ህዝብ ላይ ጭፍጨፋ በመፈጸም የልቡን ካደረሰ በኋላ ሰሞኑን በማህበራዊ ትስስር ገጽ ላይ “በአፋር ልዩ ሃይልና ሚሊሻ ጥቃት ተፈጽሞብኛል” የሚል ፕሮፖጋንዳ መንዛት ተያይዞታል።
የሽብር ቡድኑ የአፋር ህዝብን ውለታ በመዘንጋት በክልሉ በሚገኙ ልዩ ልዩ ዞኖች ማለትም በኪልበቲ ረሱ ዞን በራህሌ ወረዳ ዓላ ቀበሌ ዓሰዳ በተባለ አካባቢ ሐምሌ 29 ቀን 2013 ዓ.ም በፈንቲ ረሱ ዞን በጋሊኮማ ጊዜያዊ መጠለያ ተጠልለው የነበሩ 240 ንጹሀንን መጨፍጨፉ ይታወሳል። እንዲሁም በፈንቲ ረሱ ዞን ኡዋ፣ ያሎ፣ አውራና ጎሊና ወረዳዎች ላይ ወረራ እና ንፁሀን አርብቶ አደሮችን፣ ህፃናትን፣ ሴቶችን፣ የሀገር ሽማግሌዎችንና የሀይማኖት አባቶችን ዘግናኝ በሆነ መልኩ በመጨፍጨፍ ለአፋር ህዝብ ያለውን ጥላቻ፣ ንቀትና አረመኔያዊነት በተግባር ካረጋገጠ በኋላ አሁን የአዞ እንባውን በማዝነብ ላይ ነው።
የአፋር ህዝብ በባህሪው እና በባህሉ በፍቅር ለመጣ መሬት ሆኖ የሚቀበል፣ በሀይል ለመጣ ደግሞ ልክ እንደ ኤርታአሌ እሳተ ጎመራ ፍም እሳት ሆኖ የሚለበልብ ታሪክ ያለው ህዝብ መሆኑን እንዴት መርሳት ይቻላል? ኤርታአሌን በሩቁ መመልከት እንጂ በእጅ መንካትን ወትሮውንም የማይፈቅዱት አፋሮች የሽብር ቡድኑ ክልሉን በለመደው ሁኔታ ያሻውን ለማድረግ ሙከራ ቢያደርግም አይቀጡ ቅጣት ተቀጥቶ በርካቶች ለሞት፣ ከፊሉ ለምርኮ፣ የተቀረው ደግሞ እግሬ አውጭኝ ብሎ እንዲፈረጥጥ መደረጉ የቅርብ ጊዜ ትውስታ ነው፡፡
ቡድኑ ያወጣውን መግለጫ በአፋር ክልል ባካሄደው ወረራ እና በፈጸመው ጭፍጨፋ በቀጥታ ተጎጂ የሆኑት ንጹሃን መሆናቸው ዓለም ያወቀው፤ ጸሃይ የሞቀው ሆኖ ሳለ አሁንም “ጉዳይ ያለኝ ከሰላማዊ ሰዎች ጋር ሳይሆን ከታጣቂው አካል ጋር ነው” በማለት የለመደውን ፕሮፖጋንዳ ነዝቷል።
ቡድኑ በአፋር ህዝብ ላይ የፈጸመውን ጭፍጨፋ ከአፋር ህዝብ በላይ ምስክር ሊገኝ በማይቻልበት በዚህ ወቅት የአፋርን ህዝብ ወዳጅ አድርጎ ማሰብ ከእውር ድንብርብርነት ተለይቶ ሊታይ አይችልም። የሽብር ቡድኑ ዲስኩር የአፋር ህዝብ ራሱን ከጥቃት ለምን ተከላከለ የሚል ካልሆነ በስተቀር ጉዳዩ ‘የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም’ እንደሚባለው ነው።