በሁከቱ የተሳተፉ አካላት በህግ እንዲጠየቁ የሚደግፉ መሆናቸውን በጂግጂጋ ከተማ ምሁራን ገለጹ - ኢዜአ አማርኛ
በሁከቱ የተሳተፉ አካላት በህግ እንዲጠየቁ የሚደግፉ መሆናቸውን በጂግጂጋ ከተማ ምሁራን ገለጹ
ጅግጅጋ ነሀሴ 9/2010 በሶማሌ ክልል ተፈጥሮ በነበረው ሁከት የተሳተፉና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈጸሙ አካላት በህግ እንዲጠየቁ የሚደግፉ መሆናቸውን በጅግጅጋ ከተማ የሚኖሩ ምሁራን ገለጹ፡፡ ምሁራኑ ይህንን የገለጹት በክልሉ ተከስቶ በነበረው ሁከት ዙሪያ በጅግጅጋ ከተማ ባከሄዱት ውይይት ማጠቃለያ ላይ ባወጡት የጋራ አቋም መግለጫ ነው፡፡ በጅግጅጋ ፣ ደገህቡር፣ጎዴ፣ዋርዴር፣ ቀብሪደሀርና ሌሎች ከተሞች ተፈጥሮ በነበረው ሁከት በሰው ህይወትና ንብረት ላይ በደረሰው ጉዳት ምሁራኑ የተሰማቸውን ሀዘን ገልጸው ድርጊቱ በመኮንን ሰላም ወዳዱን የክልሉን ህዝብ እንደማይወከል ተናግረዋል። መንግስት በሁከቱ የተሳተፉና ኢ-ሰብአዊ ድርጊት የፈጸሙ አካላትን በህግ ለመጠየቅ የተጀመረው ስራ እንደሚደግፉም በአቋም መግለጫቸው አረጋግጠዋል። ምሁራኑ ህገመንግሰቱ በሚፈቅደው አግባብ የክልሉን ሰላምና መረጋጋት ለመመለስ በተሰማራውን የሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ህብረተሰቡ በጥርጣሬ እንዲመለከተው የሚሰሩ አካላት ተገቢ ባለመሆኑ እንደሚቃወሙ ገልጸዋል፡፡ በክልሉ ሰላምና መረጋጋት ለማምጣት እና የህብረተሰቡን ጋራ እሴቶች የሆኑ አብሮነትና ወንድማማችነትን ለማስመለስ የበኩላቸውን እንደሚወጡም ምሁራኑ በአቋም መግለጫው አስታውቀዋል። የክልሉ ልዩ ኃይል ዋነኛ ስራቸው የማህበረሰቡን ሰላም ማስጠበቅ በመሆኑ ይህንን ኃላፊነት በተገቢ መወጣት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡ በክልሉ ተፈጥሮ በነበረው ሁከትና ረብሻ ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች መልሶ ለማቋቋም ለሚደረገው ድጋፍ የማሰባሰብ ስራ ግንባር ቀደም ተሳታፊ እንደሚሆኑም ምሁራኑ ገልጸዋል። በሀገሪቱ የተጀመሩ የለውጥ እንቅስቃሴዎች ለማጠናከር የሚጠብቅባቸውን እንደሚወጡም ምሁራኑ በጋራ አቋም መግለጫ አመላክተዋል፡፡ በውይይቱ የሀገር መከላከያና ሌሎችም የጸጥታ አካላት ተሳትፈዋል፡፡