ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ለዘማች ቤተሰብ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቀሱ ድጋፍ ተደረገ

ጋምቤላ፤ መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) የጋምቤላ ክልል ትምህርት ቢሮ በህልውና ዘመቻው በመሳተፍ ላይ ለሚገኙ የዘማች ቤተሰብ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።

ዛሬ በቢሮው የተደረገው የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ 1 ሺህ 200 ተማሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሙሴ ጋጅት ድጋፉን ሲያስረክቡ እንደገለጹት፤  ድጋፉ በህልውና ዘመቻው በመፋለም ላይ ለሚገኙ የልዩ ኃይል አባላት ተቋማዊና ህዝባዊ ደጀንነትን ለመግለጽ ነው።

የተለገሰው ድጋፍ ከ400 ሺህ ብር በላይ ግምት ያለው 10 ሺህ የመማሪያ ደብተርና አስር ፓኬት እስክብሪቶ መሆኑን አስታውቀዋል።

"በቀጣይም ለዘማች ቤተሰቦች የሚደረገው ድጋፍ ተጠናክሮ ይቀጥላል" ብለዋል።

በድጋፉ ርክክቡ ላይ የተገኙት የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽነር አቡላ ኡቦንግ ፤የክልሉ ትምህርት ቢሮ ለዘማች ቤተሰቦች ያደረገው ድጋፍ አርአያነት ያለው መሆኑን በመግለጽ ምስጋና አቅርበዋል።

እንደ ኮሚሽነሩ ገለጻ አሸባሪው የህወሓት ቡድን የከፈተውን ጦርነት ለመቀልበስ በተጀመረው የህልውና ዘመቻ የክልሉ ልዩ ኃይል አባላት ከሌሎች የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን በግንባር እየተፋለሙ ይገኛሉ።  

ለህልውና ዘመቻው ስኬት የተጀመረው የመተባበር መንፈስ መጠናከር እንዳለበት አሳስበዋል።

የክልሉ ልዩ ኃይል አዛዥ ኢንስፔክታር ኮንግሪክ ፤ለዘማች ልዩ ኃይል አባላት ልጆች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ በመደረጉ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም