ቀጥታ፡

"አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ"

መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) "አዲስ የሚመሰረተው መንግስት ካለፈው በመማር የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት ቅድሚያ ሰጥቶ ይሰራል የሚል እምነት አለኝ" ሲሉ የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር ዶክተር አረጋዊ በርሄ ተናገሩ።
ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ነጻና ፍትሃዊ እንዲሁም በህዝብ ዘንድ ተዓማኒነትን ያተረፈ ምርጫ አካሂዳለች ሲሉም ተናግረዋል።

በዚህም በመጪው መስከረም 24 በህዝብ ይሁንታ አግኝቶ በምርጫ ያሸነፈው አዲስ መንግስት ይመሰረታል ብለዋል።

ዶክተር አረጋዊ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ አንዳሉት አዲስ የሚመሰረተው መንግስት በኢትዮጵያ ከዚህ ቀደም አጋጥመው ከነበሩ የፖለቲካ ስህተቶች ብዙ ነገሮችን ይማርበታል።

ከዚሀም የህዝቡን ጥያቄ ለመፍታትና የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት በቁርጠኝነት ይሰራል የሚል እምነት አለኝ ብለዋል።

የፊታችን መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ የሚመሰረተው መንግስት የህዝብን ፍላጎት ለማሟላት ቅድሚያ ሰጥቶ የሚሰራ እነደሚሆን እናምናለን ነው ያሉት።

በሰላማዊ የምርጫ ሂደት አልፎ መንግስት መመስረት ለቀጣዩ የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ስርአት ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም ዶክተር አረጋዊ  ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ህዝብ አምኖበት የሰጠውን ድምፅ በማክበር የአገሪቷን መጻዒ ዕድል የተሻለ ማድረግም ከአዲሱ መንግስት የሚጠበቅ ስራ ነው ብለዋል።

በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ውድድር ከተደረገባቸው 436 የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በ410ሩ አሸናፊ መሆኑ ይታወቃል።

ቀሪዎቹ ወንበሮች በተፎካካሪ ፓርቲዎችና በግል ተወዳዳሪዎች የተያዙ ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም