የአሜሪካ ጫና የህወሓትን ህልውና ለማስቀጠል ከመሻት የመነጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአሜሪካ ጫና የህወሓትን ህልውና ለማስቀጠል ከመሻት የመነጨ ነው
ሀዋሳ፤ መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) የአሜሪካ ጫና በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ የህወሓትን ህልውና ለማስቀጠል ከመሻት የመነጨ መሆኑን በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ ሳይንስና አለም አቀፍ ግንኙነት ምሁራን ተናገሩ፡፡
አንዳንድ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ለነርሱ የሚታዘዝ ደካማ መንግስት እንዲኖር እንደሚፈልጉ ነው ምህራኑ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት የገለጹት።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁር ዶክተር ንጉስ በላይ እንዳሉት፤ አሜሪካ በኢትዮጵያ ላይ የማዕቀብ ጫና ለማሳደር የምትሞክረው ለአካባቢው ሰላምና ሰብዓዊ መብት መከበር በማሰብ ሳይሆን ታላላቅ ሀገራዊ የለውጥ ምዕራፎችን ለማደናቀፍ ነው።
በኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናት ላይ የቪዛ ክልከላ ማዕቀብ ሲጣልም ኢትዮጵያውያን ለመጀመሪያ ጊዜ ሊባል በሚችል ደረጃ ፍትሐዊ ምርጫ ለማካሄድ እየተዘጋጁ ባሉበት እንዲሁም ታላቁ የህዳሴው ግድብ ሁለተኛ ዙር ሙሌት በስኬት በተጠናቀቀበት ወቅት መሆኑን አስታውሰዋል።
ከአሸባሪው ህወሓት ጋር ተደራደሩ በሚል ጫና ለማሳደር እየተደረገ ያለው ጥረት ቡድኑ በምስራቅ አፍሪካ የአሜሪካና አጋሮቿ ታማኝ ጉዳይ አስፈፃሚ በመሆኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ህልውናው ቀጣይ እንዲሆን በማሰብ መሆኑን አስረድተዋል።
አሜሪካ የምትከተለው በራስ ጥቅም ላይ ብቻ የተመሰረተ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲዋ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተቀባይነት እያጣ መሆኑን ጠቁመዋል።
በዩኒቨርሲቲው የፖለቲካ ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ አወል አሊ በበኩላቸው፤ ምዕራባውያኑ ኢትዮጵያ ውስጥ ለነርሱ የሚታዘዝ ደካማ መንግስት እንዲኖር እንደሚፈልጉ ተናገረዋል።
የህዝብ ይሁንታ ያለውን የኢትዮጵያ መንግስት በጫና ህወሓት የሽብር ቡድን ጋር እንደራደር ማድረግና በሀገሪቱ የውስጥ ፖለቲካ ውስጥ ተፅዕኖ ፈጣሪ እንዲሆን ማስቻልን እንደ ስልት እየተጠቀሙበት ነው ብለዋል።
ከሰሞኑ የአሜሪካ መንግስት እያደረገ ያለው ጫና ይህንን አጀንዳ ለማስፈፀም ያለመ መሆኑን ገልጸው፤ ይህ ድርጊታቸው ከህግና ሰብዓዊ መብትም ሆነ ሞራል አኳያ መሠረት የሌለው መሆኑን አስረድተዋል።
አንዳንድ ምዕራባዊያን በመሪዎቻቸውም ሆነ በመገናኛ ብዙሃኖቻቸው አማካይነት የተሳሳቱ መረጃዎች በማራገብ ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማምታታት እየጣሩ መሆኑን አመልክተዋል።
አሜሪካን ማዕቀብ ለመጣል የምታደርገው እንቅስቃሴ ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የፃፉት ደብዳቤ የኢትዮጵያን ጠንካራ አቋም፣ የህዝቦቿን ክብርና አልምበረከክም ባይነትን በግልፅ የሚያሳይ መሆኑንም አወስተዋል ምሁሩ።
ኢትዮጵያ ዴሞክራሲና ፍትህ ምርጫ ካካሄደች በኋላ በህዝብ የተመረጠ መግስት ለመመስረት በዝግጅት ላይ መሆኗን ተናግረዋል።
ከምንጊዜውም በላይ ከሚመሰረተው መንግስት ጎን በመቆም ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ እንድትቀጥል መስራት የሚጠበቅብን ወቅት ላይ ነን ብለዋል።