ቀጥታ፡

በኢትዮጵያ የተካሄደው ስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ለቀጣይ ምርጫዎች የዴሞክራሲ እርሾ የሚሆን ነው

አዲስ አበባ መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) በኢትዮጵያ የተካሄደው ስድስተኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫ ለቀጣይ ምርጫዎች ዴሞክራሲያዊ ሂደት እርሾ ይሆናል ሲሉ የተለያዩ የተፎካካሪ ፓርቲ አመራሮች ተናገሩ።

ኢዜአ ያነጋገራቸው የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች የምርጫ ክንውን የአገር ህልውና ሲኖር በመሆኑ ከየትኛውም ጉዳይ የሚቀድመው የኢትዮጵያ ሉአላዊነት መሆኑን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ መልከ ብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በተደቀነባት ወቅት በተደገረው 6ኛው ዙር ጠቅላላ ምርጫም ውጤቱ ሳይሆን የሚያሳስበን የኢትዮጵያ የዴሞክራሲ ልምምድና የህልውናዋ ቀጣይነት ነው ብለዋል።

የአዲስ ትውልድ ፓርቲ ዋና ፀሐፊ አቶ ክፍለማርያም ሙሉጌታ ኢዜአ እንዳሉት ባሳለፍነው ሰኔ ወር የተካሄደው ምርጫ ከነበሩ ምርጫዎች የተለየና ህዝብ በነቂስ ወጥቶ የመረጠበት ልዩ አጋጣሚ እንደሆነ ገልጸዋል።

የምርጫው ሂደት ለቀጣይ ምርጫዎች የዴሞክራሲ እርሾ የሚተው ጥሩ ጅምር የታየበት መሆኑንም የፓርቲዎቹ አመራሮች አንስተዋል።

የራያ ራዩማ ፓርቲ የውጭ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጌታቸው ከበደ፤ 6ኛው ጠቅላላ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ግልጽ፣ ተቋማዊ ነጻነት የነበረበት እንደነበር አንስተዋል።

ቅሬታ የቀረበባቸው አካበቢዎች በገለልተኛ አካል ተጣርቶ ድጋሚ ምርጫ መደረጉ፣ ገዥው ፓርቲ እንደማንኛውም ፓርቲ በእኩል ዕጣ መወዳደሩና የፓርቲዎች የዕኩል ተደማጭነት ከወትሮ ምርጫዎች የተለየ አድርጎታል ብለዋል።

ምርጫው ግልጽ፣ ተጠያቂነት የሰፈነበት፣ ነጻና ፍትሃ እንደነበርም አስታውሰዋል።

የሕዳሴ ፓርቲ ዋና ጸሃፊ አቶ ሱራፌል እሸቱ፤ ምርጫው ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ነጻ እንደነበር ገልጸው ቀደም ሲል ሲካሄዱ የነበሩ ምርጫዎች ግን ለይስሙላ የተደረጉ ነበሩ ብለዋል።

ወደ ምክር ቤት የገቡ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና በመንግሰት እርከን የሚሳተፉ ፖለቲከኞች መንግስትን ክፍተት የሚሞሉበት እና ለዴሞክራሲው መጎልበት አስተዋፅኦ የሚያደርጉበት ይሆናል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም