ኮርፖሬሽኑ ባዮ ጎልድ የተባለ ኦርጋኒክ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መዘጋጀቱን ገለጸ - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ ባዮ ጎልድ የተባለ ኦርጋኒክ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መዘጋጀቱን ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 14/2014 (ኢዜአ) የኢትዮጵያ የግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ባዮ ጎልድ የተባለ ኦርጋኒክ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መዘጋጀቱን ገለጸ።
ኮርፖሬሽኑ ከአሜሪካው ኦርጋኒክ ኢንተርናሽናል ኤል ኤል ሲ ኩባንያ ጋር በመተባበር ማዳበሪያውን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት መዘጋጀቱን አስታውቋል።
ማዳበሪያውን ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት የተደረገውን ስምምነት በተመለከተ ሁለቱ ተቋማት በቢሾፍቱ ምክክር ማድረጋቸውን ኮርፖሬሽኑ ለኢዜአ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
በመግለጫው እንደተመለከተው ከጥራትና ምርታማነት እንዲሁም ከጤና አኳያ ባዮ ጎልድ የተባለው ኦርጋኒክ የአፈር ማዳበሪያ በዓለም ገበያ ተመራጭ በመሆኑ ወደ አገር ውስጥ ለማስገባት ዝግጅት ተደርጓል።
በዚህም መሰረት ከኦርጋኒክ ኢንተርናሽናል ኤል ኤል ሲ ኩባንያ ጋር በመተባበር የተለያዩ የአትክልት ዘሮችን ለማስመጣትና የድቃይ በቆሎ አቅርቦት ለመጀመር ውይይት መጀመሩን የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈጻሚ ክፍሌ ወልደማሪያም ገልጸዋል።
የግብርና ሚኒስቴር ተወካይ አቶ ገርማሜ ጋሩማ፤ የአፈር ማዳበሪያው በመንግስት በኩል ተቀባይነት በማግኘቱ ለማስገባት ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።
በመሆኑም ባዮጎልድ የአፈር ማዳበሪያ በግብርና ኤክስቴሽን በኩል እንደ አማራጭ ይቀርባል ብለዋል።
በመድረኩ የተገኙት የኦርጋኒክ ኢንተርናሽናል ኤል ኤል ሲ የቴክኒክ አማካሪ ዶክተር አሰፋ አዳነ ስለ ባዮጎልድ ጠቀሜታና ተያያዥ ጉዳዮች ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢትዮጵያ ግብርና ስራዎች ኮርፖሬሽን ሙከራ ተደርጎባቸው ውጤታማነታቸው የተረጋገጠና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያስችሉ አዳዲስ የግብርና ግብአቶችን ለአርሶ አደሮችና ባለሃብቶች በማቅረብ ላይ ይገኛል።